የአዲስ አበባ ውሾች
በራሴላስ ወልደ ማርያም
ክፍል አንድ
“ውሻ በውሻ ላይ ከጨከነ ሰው በውሻ ላይ ቢጨክን ምን ይገርማል?” አለ ሉሉ ዳንኤል ክብረት
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሊወርዱ ሰባት ወር ሲቀራቸው በሀምሌ 2010 ዓመተ ምህረት አቶ ዳንኤል ክብረት አንድ በውሾች ገጸ ባህሪ መስለው ያሳተመት መጽሀፍ አለ። ይህንን መጽሐፍ በቻግኒ ዩቲዩብ የተተረከውን አደመጥኩት። መጽሐፏ የፓለቲካ ስላቅ (Political satire) እንደሚባለው ነው።
አቶ ዳንኤል ክብረት የጠቅላይ ሚኒስቴር አማካሪ ሆነው ከመሾማቸው በፊት ዘላለማዊውን የክርስቶስን መንግስት በመስበክና በደራሲነት ይታወቁ ነበር። ለምድራዊ ሀያላን ግልጋሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ ግን ለክርስቶስም ለድርሰቱም ገዜ አላገኙም። ራዶቫን ካራዲዝች (Radovan Karadzic) የሰርበያ ዜጋ ከቦዝንያ ጦርነት በፊት የተዋጣለት ገጣሚ ነበር። በኋላ በቦዝንያ ጦርነት የተካፈለና በዘር ማጥፋትም ተከሶ ከገጣሚዎች አለም ተለየ። የኔም ስጋት አቶ ዳንኤል “የአዲስ አበባ ውሾች” ብለው ያሳተሙት መጽሐፍ የመጨረሻቸው ይመስለኛል።
የዚህ ጽሁፍ አላማ አቶ ዳንኤል ሳይሆኑ ይህ መጽሀፋቸው ነው። የስነ ጽሁፍ ችሎታቸው እንደ ፓለቲካቸው አወዛጋቢ አይደለም። አማርኛን አሳክቶ የመጠቀም፣ የማያልቅ የአዛውንቶች ተረት በመጽሀፋቸው ውስጥ ነስንሰውና አዋህደው ማቅረብ ይችላሉ። ለኔ አቶ ዳንኤል ክብረትን የስነ ጽሁፍ ችሎታቸውን ያሳዩበት መጽሐፍ ካለ “የአዲስ አበባ ውሾች” ብለው ያሳተሙት ነው።
መጽሐፉ እንዲህ ብሎ ይጀምራል፣
“አዲስ አበባ፣ በደሳለኝ ሆቴል ጎን ታጥፎ ወደ ጎዳና በሚወስደው ስላች አስፓልት አንድ ወገቡ ላይ ልብስ የለበሰ ውሻ ልቡ እስኪጠፋ ይሮጣል። ከኋላው ደግሞ መሳሪያ የታጠቁ ሁለት ፓሊሶች ድንጋይ አየወረወሩ ያባርሩታል። እነርሱ ከኋላ ሲወረውሩበት በባለሥልጣናቱ ቤት በር ላይ ለጥበቃ የተቀመጡት ሌሎች ወታደሮች ይቀባበሉበታል። እርሱ ደግሞ ልቡ ከእግሩ እየፈጠነ ይፈተለካል። ወደ የት እንደሚሄድ አያውቅም፣ በየት በኩል እንደሚሮጥ አያውቅም። ብቻ ይሮጣል።እንግዲህ በጎዳና ላይ በእግሩ ሲዳክር ለመጀመሪያ ግዜው ነው። መኪና ተመድቦለት፣ ወንበር ተደልድሎለት ከተማዋን በክብር ሲዞርባት እንዳልነበር ዛሬ ከተማዋ ራሷ ትዞርበት ጀመር።
ወደ አትላስ ሆቴል የሚወስደው አስፓልት መንገድጋ ደረሰና ቆመ። ልትወልቅ እግሩ ሥር ደርሳ የነበረችው ልቡ ወደ ሆዱ ተመለሰች። ግራና ቀኙን ሲያማትር አንድ ቀዥቃዣ መኪና በአጠገቡ አጓርቶ አለፈ። ወደ ኃላ አፈገፈገና የአንዱን ግቢ አጥር ተጠጋ። ከግቢው ውስጥ ያለ ውሻ እንደ መብረቅ ሲጮህበት በድንጋጤ ጎዳናው ውስጥ ገባ። ውሻ በውሻ ላይ ከጨከነ፣ ሰው በውሻ ላይ ቢጨክን ምን ይገርማል አለ በልቡ።” መጽሐፏ ከመከበር፣ ከመፈራት፣ከምቾትና ድሎት የወደቀ የባለ ስልጣን ውሻ ፌዴራል ሲያባርው ነው የሚጀምረው። ይሁንና ብዙ ቁም ነገሮችን በውሾቹ አፍ እያስገባ አቶ ዳንኤል የልቡን ተናግሮ ነበር። አሁን እሳቸው የሚያማክሩት ስርአት እንኳን በውሻ አፍ በወፍም አድርጎ እንዲህ አይነት ጽሁፍ ማሳተም አይፈቅድም።
ይህ መጽሐፍ የተዋጣለት ብቻ ሳይሆን የትንቢትም መጽሀፍ ነው። አቶ ዳንኤል የእንባገነን ስርአት አገልጋዬች ህይወት እንዴት እንደሚደመደም ያሳዩበት ቆንጆ መጽሀፍ ነው።
አንድ ሉሉ የሚባል ቅምጥል ውሻ ጌታው “በሁለት እጅ የማይነሱና” የሚፈራ ባለ ስልጣን ነበር። በድንገት ከስልጣን ተባሮ ወደ ቃሊቲ በወረደ ማግስት ቤቱን ለቃችሁ ውጡ ተብለው ቤተሰቡ ሁሉ ተባሩሩ። ልክ ሰሞኑን የአቶ ታዬ ደንድአ ቤተሰቦች እንደተባረሩት ማለት ነው።
የአዲሱ ባለስልጣን ጠባቂዎች ደግሞ ቤተሰቦቹ ጥለውት የሄዱትን ሉሉ የሚባለውን ታማኝና ቅምጥል ውሻ በድንጋይ ልቡ እስከሚፈርስ ሲያሯሩጡት ታሪኩ የሚጀምረው። ሉሉ መከራው መጥቶ ሲወድቅበት “ጌታው በበሉት እጸ-በለስ እሱ ለምን ከገነት እንደተባረረ” አልገባውም። ይሄም ይመጣል ብሎ አስቦ ወይንም የስነ ልቦና ዝግጅት አድርጎም አያውቅም። ድንገት መከራው ዱብ ሲልበት የነ ሉሉ ዘበኛ የሚያንጎራጉሩት ትዝ አለው።
“መከራ ሲመጣ አይነግርም ባዋጅ
ሲገሰግስ አድሮ ቀን ይጥላል እንጂ” አለ።
ይህንን የዘበኛቸውን እንጉርጉሮ ሉሉ ብዙ ግዜ ሰምቶታል ይሁንና ምን ማለት እንደሆነ እስከዚህ ቀን አላስተዋለም ነበር። ይህ ጌታውን የተማመነ ቅልብና ክፉ ውሻ አሁን መንገድ ላይ ተጥሎ አንዱ በድንጋይ፣ አንዱ በመኪናው ጡሩንባ፣ ሌላው በጎማው ለጥቂት ሲስተው ሁሉ ነገር እንደ ብርሀን ግልጽ ብሎ ታየው። ከዱላው፣ ከረሀቡና ከመቆሸሹ ጋር ተደርቦ ጸጸት ልቡ ይገባል።
ለካ ይላል ሉሉ “አሪፍ ውሻ ማለት ጥሩ ክፉ ውሻ ነው እንደማለት ነው። አንተ ክፉ ውሻ ከሆንክ ለጌታህ አሪፍ ውሻ ነህ። ትናከስላቸዋለህ፣ ትጮህላቸዋለህ፣ አላፊ መንገደኛውን ታስደነብርላቸዋለህ ታስፈራራላቸዋለህ ለሌሎች ክፉ ስትሆን ለጌቶች ምርጥ ውሻ ትሆናለህ። በኋላ ግን እዳው አንተው ላይ ይወድቃል። በመጨረሻው አንተው ትወረወራለህ፣ ለጂቦቹም ተላልፈህ ትስጣለህ” ይላል።
ሉሉ የተቀማጠለ የባለ ጊዜ፣ የባለ ስልጣን ውሻ ነበር። ይህ ውሻ የሚፈራ፣ ከልጆች እኩል አማርጦ የሚበላ፣ ለባለስልጣኑ የተመደቡት ፌዴራሎች ገላውን የሚያጥቡት፣ ባለስልጣኑን ለማስደሰት የሚመጡ ሀብታምች ሁሉ እኔ እኮ ውሻ እወዳለሁ የሚያስብል፣ ልብስና መኝታ ቤት ያለው፣ በ v8 ላንድ ክሩዘር ተጭኖ ህዝብን በመስኮት እያየ አዲስ አበባን የሚዞር ቅምጥል ነበር። ይሁንና የኢህአዴግ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነበርና ይህ የተከበረ ባለስልጣን ድንገት ከስልጣን ተባሮ ታሰረ። ማለትም ልክ እንደነ ጠቅላይ ሚኒስቴር ታምራት ላይኔ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር ስዬ አብረሀ፣ የደህንነት ምክትል ሀላፊ አቶ ኢሳያስ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ እብዲ ኢሌ፣ ወይንም የቅርቦቹ ሚኒስቴር ዴታዎች እንደነ አቶ ታዬ ደንደአ እና አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደ ማለት ነው። ስም አይጠራ እንጂ ሉሉ እንዲህ ይፈሩ የነበሩ ባለስልጣን ውሻ ነበር።
ያ “በሁለት እጅ የማይነሳ” የነበረው፤ የሚፈራው፣ ሁሉ የሚርድለት ባለ ስልጣን ሉሉን፣ ሚስቱንና ልጆቹን በትኖ ወደ ማአከላዊ ምርመራ ተሸኘ። ባለስልጣኑ በበላው እጸ-በለስ በ24 ሰአታት ውስጥ ሁሉም መንገድ ላይ ወጥተው ተጣሉ።
ይህ ውሻ ለብቻው መንገድ እንኳን አቋርጦ የማያውቅ ነበር። ፌዴራል ፓሊስ አጅቦት ከግቢ ሲወጣ ፌዴራሉን ያየ ባለ መኪና አቁሞለት ተፈርቶ የሚሻገር ነበር። አሁን መንገድ ላይ ሲወጣ ፍጥነቱን ሳይቀንስ ለጥቂት የሚስተው፣ ዝሆንን የሚያደነቁር ጡሩንባ የሚነፋበት ከተማ ውስጥ ዱብ አለ። ከአንዱ ጎማ ሲያመልጥ ሌላ በጡሩምባና ጎማ እየሳተው ወደ አትላስ አካባቢ ይደርሳል። እዛ መንገድ ላይ የተጣለ ንካው የሚባል የከተማ ውሻ ያገኛል። ሉሉ ይህ ንካውን ሲያይ ለምን “በአጥንቱ ላይ ቆዳ ጣል አደረገ፣ ለምን አልታጠበም፣ ለምን ቆሸሸ፣ ሽታውስ ለምን አፍንጫ ይቆርጣል፣ ጉስቁልናው የሚያስፈራ፣”ስጋ ቅን ውሻ” ከየት መጣ ብሎ ሰያስብ ንካው ጆካው ብሎ በተረብ ተዋወቀው።
ንካው ደግሞ ይህ የተመቸው በጀርባው ላይ ልብስ የለበሰ ውሻ በቅርብ ከሙስና ሰፈር የተባረረ ቅምጥል መሆኑን ገብቶታል።
ይህ “ስጋ ቅብ ውሻ ጆካው” ብሎ በተረብ ሉሉን ይተዋወቀዋል። የዳንኤል ክብረት መጽሐፍ የነዚህ የሁለት አለም ውሾች ጭውውት ነው። በመሀከሉ እንዲሁ እንደ ሉሉ ግዜ የጣላቸው ውሾች ይቀላቀላሉ። ሁለተኛው በጆሴ ሞሪኒዮ የተሰየመው “ጆሲ” የሚባል ውሻ ነው፣ ሶስተኛው ባለቤቱ ከኒዮርክ አምጥቶ ሲከስር ጥሎት የሄደው “ኮለምበስ” የሚባለው ውሻ ነው። አራተኛው ደግሞ ከአላህ በላይ ለመንግስት ጠበቃ የነበሩት በመጨረሻ የተባረሩት የሀጂ ኤልያስ “ባሲል” የሚባል ውሻ ነው። አንዱ ደግሞ በርቀት የተወረወሩ የደብር አለቃ “ውቃቤ” የሚባል ውሻ ታሪክ ነው። ስም አይጥራ እንጂ የቱጃሩ አረብም ውሻ አለ።
እነዚህ ውሾች ምግብ ፍለጋ ሲንከራቱ የቤተ መንግስቱ ቅልብ ሶሎግ ውሾችን፣ ከሰፈራችን ካዛንቺስ ውጡልን የሚለው “ሲባ” የሚባለው የብሄር ነጻ አውጪ ውሾች መሪን፣ በእስር የተጣሉ ውሾችን፣ የሚሰልሏቸው የሚከታተሉዋቸው የመንግስት ታማኝ ውሾች ያገኛሉ። በታሪኩ ውስጥ ብቅ እያሉ ትርክቱን አሳምረውት የሚያልፍ ብዙ ውሻች ናቸው። የቱጃሩ አረብ ውሻም፣ የዲያስፓራውም እንግሊዘኛ ተናጋሪ ጆሲም፣ የደብር አለቃውም ውሻ ግዕዝ ጣል ጣል እያደረጉ ታሪካቸውን እያወሩ ፈተናቸን ይጋፈጣሉ
እነዚ ሁሉ የባለ ጊዜ ጥሩ ውሾች ነበሩ። እነሱ ከውሻነት ስራ ያለፈ ሀጥያት አልሰሩም ይሁንና ጌቶቻቸው በበሉት እጸ-በለስ ፍዳ የወረደባቸው ነው። ይህ እንግዲህ በውሾች ይመሰል እንጂ የእንባገነን አገልጋዮች የህይወት ታሪክ ነው። ሉሉ የባለ ጊዜው ውሻ ምሬት የሁሉንም ጸጸት ይገልጸዋል።
ይህ ትርክት የዛሬ የበርካታ የመንግስት አጃቢዋች፣ የፌዴራል ፓሊሶች፣ የመከላከያ አባላት፣ የጠቅላይ መኒስታር አማካሪዎች፣ የብአዴን ባለ ስለስልጣናት፣ የገቢና የታክስ ስራተኞች፣ የቀበሌ ዘበኞች፣ የደንብ አስከባሪዎች፣ የአድማ በታኝ ታጣቂዎች፣ የትራፊክ ፓሊሶች፣ የሚኒስቴሮች፣ የጄኔራሎች፣ የጋዜጠኞች፣ የአቃቤ ህጎች፣ የዳኞች፣ የአክቲቪስቶች፣ በየ መንደሩ ቁጭ ብለው የሚሰልሉ ጆሮ ጠቢዎች፣ የተደራጁ የቤት አፍራሾች ግለ ትርክት ነው። ሉሉ እንዳለው በጌቶቻቸው ጥሩ ውሾች ለመባል ክፉ ውሻ የሆኑ ብዙ ሚሊዮኖች ታሪክ ነው።
ሰዎች ለአለቆቻቸው ጥሩ ውሻ ለመባል ህዝብ ይናከሳሉ፣ በቆመጥ ህዝብን ያንቆራጥጣሉ፣ ህዝብን ዘቅዝቀው ይገርፋሉ፣ በሀሰት ሰነድ ህዝብን ይከሳሉ፣ የታክስ ክፍያ በማጋነን ጉቦ ይጠይቃሉ ወይንም የሰው ጉሮሮ ይዘጋሉ፣ ፍርድ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ፍትህን አጣመው በንጹሀን ይፈርዳሉ፣ ጋዜጠኛ ለጌቶቹ ጥሩ ውሻ ለመባል የውሸት ዘጋቢ ፊልም ይሰራሉ። የጎረቤቶቻቸውን ቤት በ24 ሰአት አፍርሱ ብለው ቆመጥ ክላሽ ይዘው የሚያስጨንቁ ይሆናሉ።
አቶ ዳንኤል ፈርተው ራድዋን፣ ሽመክት፣ ሀጎስ፣ ደምመላሽ፣ቀልቤሳ፣ መሀመድ፣ ጢሞቲዎስ፣ ብርሀኑ፣ የቀበሌ ሊቀመንበር፣ ሚንስቴር፣ የልዩ ጥበቃ ሻለቃ እከሌ፣ የገቢዎች ኦዲተር ወይዘሮ እንትና ማለት ስለፈሩ ሀሳቡን ሁሉ ለውሾች ሰጥተው ውሾቹን እውነቱን አናግሯቸል።
ሰው ሆነው የገበት የነ ሉሉ ዘበኛ ናቸው። እሳቸው ግጥሙንና ታሪኩን በሉሉ አፍ እየመጡ ይመክራሉ።
ሉሉ ከዘበኛው የሰማውን የመንግስት ለማን ግጥም ትዝ ይለዋል።
“የተለመደ ነው የመጣ ከጥንት
ከተጠቃው መራቅ አጥቂን መጠጋት”
ንካው የተጣለ ህዝብ ሲሆን፣ ሉሉ፣ ጆሲ ይባሉ እንጂ በየቀኑ የምናገኛቸው የባለ ጊዜ የክፏ ሰዎች ታሪክ ነው። አቶ ዳንኤል በተረትና በቀልድ አዋዝተው የጻፏት የኢህአዴግ/ብልጽግና ክፏዎችን የቀን ተቀን ውሎና ተግባር ነው።
ዛሬ አንድ ነጋዴ ገቢዎች ሲሄድ አለቆቻቸውን ለማስደሰት “አሪፍ ውሻ ለመባል” ክፉ ሆነው ፊታቸውን ከስክስው ይጠብቁሀል። በክፍለ ከተማ ሀላፊዎች፣ ገቢዎች ቢሮ ኦዲተሮች፣ በህግ አስከባሪ ፓሊሶች ፉክክራቸው በጎ መስራት ሳይሆን ክፉ መሆን ነው። ገና ወደ ጠረጴዛቸው ጠጋ ስትል “ደግሞ እንዲህ ማድረግ ጀመራችሁ ብለው በወል ስም በጅምላ ለማሸማቀቅ የሚጥሩ ብዙ ናቸው።”
እራሱ የፌዴራል ፓሊስ ሆኖ ወይንም ወታደር ሆኖ ሲዘምት የሚይዘው ሰንደቅ አላማ፣ ሲሞት የሚጠቀለልበትና የሚቀበርበትን ሰንደቅ አላማ የአማቱ ጥለት ላይ በጥምቀት በአል ሲያገኛት ጥሩ ውሻ ለመባል “አንቺ ነይ! ብሎ በጥፊ የሚያልሳት ቀሚሷን የሚቀድ ብዙ ነው።
ትንሽ ኩታራ የቀበሌ ዘበኛ ለሀገሩ ያገለገለውን አዛውንት ይዘረጥጠዋል፣ አንተ ና፣ ቁጭ በል ተቀመጥ፣ ውጣ ከዚህ ሲልና ለአለቆቹ ጥሩ ውሻ ለመባል ሲጋጋጥ ይታያል። ካልሲና ሙዝ ሸጦ ነፍሱን ለማቆየት የሚጥረውን የደንብ አስከባሪ ጥሩ ክፏ ውሻ እንዲባል በዱላ ሲዠልጣት ቆሎዋን ሲደፋባት ማየት የተለመደ ነው።
ሉሉ ከገነት እንደተባረረ የገጠመው “ውሻ በውሻ ላይ ይሄንን ያህል ከጨከነ፣ ሰው በውሻ ላይ ቢጨክን ምን ይገርማል ያለው ለዚህ ነው። አንድ የፈረንጅ ፈላስፋ “ደሀ ደሀን ሲያባርረው ካየህ እግዚኦ በል። ከያዘው ምህረት አይኖረውምና” ብሎ ጽፋል።
አብሮ የኖረውን ከጎረቤቱ ቤት ገብቶ ክርስትና የበላ፣ ልጅ ስትዳር አብሮ የጨፈረ፣ ከቀብር መልስ በድንኳን አብሮ ንፍሮ የቃመ፣ ደንብ አስከባሪ ሊቀመንበር ሲባል የጎረቤቱን ቤት አስፈርስ ሲባል አረ ጡር ነው አይልም። ለማፍረስ የሚያሳየው ጭካኔን እንደ ምሳሌ ማየት ይችላል። በአንድ ሰአት ውስጥ ለቀው ባትወጣ ወየውልህ በማለት ቆመጡን የሚዞር ክፏ ሰው በከተማችን፣ በሰፈራችን ብዙ ነው።
በያዘው ዱላ አንቆራጥጥሀለሁ፣ ወይንም በታጠቀው ክላሽ አጋድምሀለሁ የሚሉ የመሀበረሰባችን ክፏ ሰዎች ታሪክ ነው አቶ ዳንኤል ክብረት በሚጣፍጥ አማርኛ የከተቡት።
ክፍል ሁለት
የአዲስ አበባ በ24 ስአት የማፍረስ ተባባሪዎች
ውቃቤ የሚባለው ጊዜ የጣለው ውሻ እኔ የሰማሁት “መንግስት በመንግስት ላይ ይነሳል ሲባል ነበር “ውሻ በውሻ ላይ ይነሳል ሲባል አልሰማሁም ነበር” ይላል። በእርግጥ በሀገራችን ውሻ በውሻ ላይ ለምን ተነሳ ብለን መጠይቅ አለብን?
የአዲስ አበባን በዚህ ፍጥነት መፍረስ ያየ የመንግስትን ብቻ ሳይሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ቀውስ ይገባዋል። ብዙ ሰው ፒያሳ በመፍረሱ ደስተኛ አይደለም፣ ይሁንና ብዙ ሰው ደግሞ የሚጣልለትን አጥንት ለመቆርጠም በማፍረስ ተሳታፊ ነው።
ለራሱ መብት መቆም ያልቻለ ማህበረሰብ በሌላው ቤት ማፍረስ ተሳታፊ ለምን ይሆናል? ለምሳሌ በከንቲባዋና ተከታዮቻቸው ይሄንን ከተማ ለማፍረስ እቅድ ካላቸው “በሉ ይቅናችሁ” ማለት ይችል ነበር። ከንቲባዋና ጭፍሮቻቸውና ዲጂኖዋቸውን ይዘው ወጥተው በአንድ ቀን አንድ ቤት አፍርሰው አይጨርሱም ነበር።ይህ ማለት ፒያሳን ለማፍረስ አስር አመት ይፈጅባቸው ነበር። ይሁንና እነ ሉሉ እንደታዘቡት ብዙ ሰው እራሱ ላይ እስከሚደርስ ክፉ ውሻ ለመሆን ይተጋል።
እግዚአብሔር “ብርሀን ይሁን አለ ብርሀንም ሆነ” በሚመስል ፍጥነት ከንቲባዋ ይፍረስ ሲሉ ከተማው ፈረሰ። ነገም በ24 ሰአት ውስጥ ሙሉ ሀገር ሲፈርስ እንደሚችል ያመላክታል። የዶዘሩ ሹፌር፣ የኤክስካቬተር ሹፌር መንገድ ለመስራት ሲቀጠር ቀስ እያለ እያረፈ ነው የሚሰራው። የአንድ ቀን ስራን ሶስት ቀን አራዝሞ ሊያስከፍል ነው የሚጥረው።
ግን ክፉ ጥሩ ውሻ ለመሆን ግን ቤቱን ለማፍረስ እናት ልጅን ይዛ እስከምትወጣ አይጠብቅም።
ባለ ዲጂኖው፣ ባለ ፋሱ፣ ባለ መዶሻው አሮጌ ቆርቆሮ፣ ብረት ለቃሚው ገንባ ቢባል ሳምንት የሚፈጅበት በአንድ ሰአት ደርምሶ አፍርሶ እራሱን ስራ ላይ ለማድረግ ለምን ተጋ ካልን። እነ ጆሴ፣ እነ ሉሉ የነ አቶ ጌታቸው አሰፋ ውሾች በነበሩበት ግዜ የሚያሳዩት ትጋት ነው።
ለጌቶቻችን ክፉ ጥሩ ውሻ ለመባል ይተጉ እንደነበረው የአዲስ አበባ አፍራሾችም እንዲሁ ሲተጉ ታዩ።
ዶዘርና ኤክስካቬተር ነጂው ቆይ ልጄን ላውጣ የምትል እናትን እንኳን ጊዜ የማይሰጥ ጭካኔ ከየት አመጣ። የኤክስካቬተሩን መቆፈሪያ በሰው ጣራ ላይ ለመጫንና ለመደምሰስ ምን አተጋው።
ይሄንን ስንረዳ የአንባገነንት ስርአት ደጋፊዎችና ምሰሶዎች እኛው እንደ ሆንን ይገባናል። ታድያ አንባገነን ስርአት በኛ ላይ ያልነገሰ በማን ላይ ይንገስ?
አቶ ዳንኤል ክብረት ተሳታፊ ሳይሆኑ ታዛቢ በነበሩበት ዘመን “ውሻ በውሻ ላይ ይሄንን ያህል ከጨከነ፣ ሰው በሰው ላይ ቢጨክን ምን ይገርማል” ብሎ ነበር።
የፒያሳ ክፍለ ከተማ ሊቀመንበር
እስቲ ፒያሳን እንይ። ፒያሳ የቀበሌ ሊቀመንበር ነበረው። የመረጣቸውና የተሾሙበት የቀበሌ ህዝብ ነበር። ይህ ሁሉ ቤት ሲፈርስና ሲበተን የፒያሳ ወረዳ ሊቀመንበር፣ የጸጥታ ጉዳይ ሀላፊ፣ የማህበራዊ ጉዳይ ሰብሳቢ የሚባሉ ብዙ ነበሩ።ከተማው ሲፈርስ እነሱ የቆሙበት ሰገነት መፍረሱን ያገናዝባሉ ይሁንና ክፉ ውሻ ሆነው ለመታየት የወጡበትን ዛፍ ክታች ቁረጡ ይላሉ።
እነ ሉሉም እንደነታዬ ደንደአ፣ እንደነ ንጉሱ ጥላሁን እስከሚጣሉ ድረስ የንካውን አለም አያውቁም ነበር።
አሁን የፒያሳ ክፍለ ከተማ ሊቀመንበር የሱን ቀበሌ ሙሉ በሙሉ አስፈርሶ ነዋሪዎቹን እንደ ጨው ዘር በአዲስ አበባ ዙሪያ በመበተኑ የሚመሩት ቀበሌም የለም። ይሁንና ክፉ ውሻ መሆን ከቀበሌ ሊቀመንበርነት አይበልጥም። ውሻ በውሻ ላይ እንዲህ ነው የሚጨክነው።
አቶ ዳንኤል ክብረት በኮለንበስ በተባለው ውሻ አንደበት ሆነው “Bad Dog is a good Dog” ያሉት ነው።
ኮለኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ከእንድ ከቢቢሲ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “እኔ እንኳን ሰው ዝንብ ገድዬ አላውቅም ብለው”፣ አለምን ጉድ አስብለው ነበር። አሁን መለስ ብዬ ሳጤነው እውነታቸውን ነው።
በእርግጥ ኮለኔል መንግስቱ ተኩሰው ወይንም ቀጥቅጠው የገደሉት ሰው የለም። ግን ቀጥቅጠው ተኩሰው የሚገሉላቸው ብዙ ተናካሽ አብዮት ጠባቂዎች ነበሩዋቸው። አዎ ሉሉ በመጨረሻው ለጌታህ ክፉ ውሻ ሆነህ በመጨረሻ ለጅብ ትጣላለህ እንዳለው እነዚህ ካድሬዎች ናቸው በቀይ ሽብር የተፈረደባቸው።
ኮለኔል መንግስቱ ባለቀ ሰአት ሶሻሊዝምን ትተው ቅይጥ ኢኮኖሚ ብለው ያውጁና ካድሬዎቻቸውን በምክር ቤቱ ሰብስበው ሶሻሊዝም እንደ ቀረና አሁን የቅይጥ ኢኮኖሚ ዘመን እንደሆነ ያስረዳሉ። ያኔ የሶሻሊስት አርበኛ ተብለው ሲሞካሹ የነበሩት ካድሬዎች ይናደዳሉ። አንዱ ደፋር ካድሬ ይነሳና “ጓድ ሊቀመንበር እኛ ለሶሻሊዝም ብለን ከህዝብ ጋር ደም ተቃብተን እንዴት አሁን ሶሻሊዝምን እንተዋለን” ይላቸዋል።
በድፍረቱ የተናደዱት ኮለኔል መንግስቱ መልሳቸው “እኔ መንግስቱ ኃይለ ማርያም ደም ተቃባልኝ አልኩህ?” ብለው ያፋጥጡታል። አዎ እንኳን ተቃባልኝ ቀርቶ ስሙንም መልኩንም አያውቁትም። የኮለኔሉ ቁርጥ ያለ መልስ እዛው እራስህን ቻል ነበር።
አሁንም አቶ አብይ ንጉሱ ጥላሁንን የታፈኑት ልጃገረዶች ተገኝተዋል በል ብዬሀለሁ፣ ጄኔራል አበባውን ህዝብ ላይ ተኩስ፣ ሴቶችን ድፈር ብዬሀለሁ እንደሚለው ጥርጥር የለም።
ካድሬው አዎ ብለውኛል ማለት አይችም ይሁንና እንደነ ሉሉ ካድሬዎቹ ከህዝብ ጋር ደም የተቃቡት የጓድ መንግስቱ ኃይለ ማርያም ጥሩ ውሻ ለመሆን ነበር። አቶ ዳንኤል ክብረት በሉሉ መንፈስ ሆነው ያመላከቱን “አንድ ውሻ ለጌታው ጥሩ ውሻ እንዲባል መንከስ፣ ማስደንበርና ክፉ መሆን አለበት።”
ከሉሉና ጆሲ ህይወት የተማርነው ለአንባገነኖች የምን ሰጠው ግልጋሎት ሲያልቅ ለጅብ መሰጠት ነው። በጨረሻ አቶ አብይም እንደ ኮለኔል መንግስቱ እኔ “ጳጳሱን ፈትሽልኝ አልኩህ፣ ዘርጥጥልኝ አልኩህ የሚል ነው።
አቶ ዳንኤል ክብረት በሚጣፍጥ አማርኛ በነ ሉሉ፣ በነ ንካው፣ በነ ጆሲ፣ በነ ኮሎንበስ፣ የካዛንቺስ ውሾች ነጻ አውጪ መሪ ሲባ በሚባሉ የውሾች አፍ በኢህአዴግ/ብልጽግና ውስጥ ስለነበሩ ለጌቶቻችቸው ጥሩ ውሻ የሆኑ ሰዎችን ታሪክ ከትበው ለታሪክ አስቀምጠዋል።
የሚገርመው ነገር ግን እናቶች “ወልደው ሳያበቁ፣ በሰው ልጅ አይስቁ የሚሉት” ዞሮ በሳቸው ትንቢቱ ተፈጸመ።
ጳጳስና ዲያቆን
ባለፈው ወደ ቤተመንግስት የተጠሩትን አቡነ ማትያስን ድንገት በቀሚሳቸው ስር ሽጉጥ ወይ ጎራዴ ይዘው ይሆናል ብለው ዲያቄን አቶ ዳንኤል ክብረት “በደንብ ፈትሸው” አሉ ተብሎ
ተነግሯል። በእርግጥ ጳጳሱ ስውር አልሞ ተኳሽ (assassin) ይሆናሉ ብለው የሚጠረጠሩ አይመስለኝም። ይሁንና ያ እሳቸው የጻፉትም የክፉ ውሻ የትንቢት በራሳቸው ላይ እንዲፈጸም እንጂ።
የሞራል ጥያቄ
ፈረንጆቹ The moral of the story የሚሉት አላቸው። የውይይቱ ጭብጥ ማለት ነው። የአዲስ አበባ ውሾች ታሪክ በ2010 እነ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ሳሞራ፣ ደምመላሽ፣ አባይ ጸሀዬን፣ አብይ አህመድን፣ ደመቀ መኮንን ትክ ብሎ ማየት በሚያስፈራበት ዘመን ነበር። አሁንም እነ ደመላሽን፣ አብይን፣ ሽመልስን፣ አበባውን፣ ተመስገን ጥሩነህን፣ አረጋ ከበደን፣ ደሳለን ጣስው፣ ብርሀኑ ነጋን ትክ ብሎ ማየት የሚያስፈራ ነው። ይሁንና እነዚህም እንደነ ሉሉ፣ ጆሲ፣ ንጉሱ ጥላሁን፣ ታዬ ደንደአ፣ ደመቀ መኮንን ወጥተው ለጅብ ይሰጣሉ። ስለዚህ የዚህ ጽሁፍ አላማ እነ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ፣ ዳንኤል ክብረት፣ አረጋ ከበደ፣ ደሳለኝ ጣስው፣ በለጠ ሞላ ቆም ብለው እኔ ለጌቶቼ ጥሩ ውሻ ለመባል፣ ህዝቤን
መንከስ አለብኝ? ብለው እንዲጠይቁ ነው?
እነ ብርሀኑ ነጋን፣ አበባው ታደሰ፣ እነ አረጋ ከበደ ብቻ ሳይሆን ከታች በየ ቢሮክራሲው የተሰገሰገ በህዝብ ላይ ክፉ ውሻ በመሆን ለመወደድ ለመሾም ለመዝረፍ እንዳይተጉ ነው።
እስቲ ነገ ጥዋት ወደ ወደ ቀበሌ ቢራችን፣ ገቢዎች ባለ ስልጣን፣ ክፍለ ከተማ ቢሮዋችን ስንገባ እኔ ለህዝብ ክፉ ውሻ እሆን ይሆን ብሎ ሁሉም እራሱን እንዲጠይቅ ነው።
ክላሽና ዱላ ተሰጥቶን ከፌዴራል ፓሊስ ተብለን ስንሰማራ፣ ከተከበረ የህግ ትምህርት ቤት ተመርቀን የተከበረ የአቃቤ ህግ ተብለን ፋይል ሲሰጠን፣ ከዩኒቨርስቲ ተመርቀን የትላልቆቹ ቴሌቭዥኖችና ጋዜጦች ዘጋቢ አንባቢ ስንሆን፣ እኔ የአቶ ዳንኤል በምናብ የሳሉት ሉሉ በሚባል ውሻ እሆን ይሆን ብሎ እንዲጠይቅ ነው።
ዳንኤል ክብረት በሉሉ አድሮ እንዳስተማረን እኔ “አሪፍ ውሻ ለመባል ለህዝቤ ክፉ ውሻ እየሆንኩ ይሆን” ብለን እራሳችንን መጠየቅ አለብን።
እነ ሉሉ በነ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ጀነራል ታደሰ ወረደ፣ በነ ተጋዳላይ አባይ ጸሀዬ፣ በነተመስገን ጥሩነህ፣ በነ ለማ መገርሳ፣ በነ አባ ዱላ፣ በነ አቦይ ስብሀት ሰፈር ሲኖሩ የተፈሩ የተከበሩ ነበሩ። ያስፈራሩ፣ ይናከሱ፣ ያስደነብሩ ነበር። ያኔ ጨካኝ ነበር። ከተባረሩ በኋላ ደግሞ “ውሻ በውሻ ላይ ይሄንን ያህል ከጨከነ፣ ሰው በውሻ ላይ ቢጨክን አይገርምም” አሉ። በግዜ ለህዝብ መቆም ነው እንጂ ጅብ ካለፈ ውሻ ቢጮህ ምን ይጠቅማል።
አሁን ማህበረሰባችን በሁለት ተከፍሏል። አንዱ ለጌታው ተናካሽ ውሻ የሆነ የብአዴን፣ የኦፒዲኦ፣ የብልጽግና ተናካሽ ውሻ፣ አድማ በታኝ ቃል አቀባይ፣ አሳሪ ፈቺ፣ ገራፊ የሆኑ። ሌላው ደግሞ ተሳዳጅ፣ ቤቱ በላዩ ላይ የሚነድ፣ ልጁ የሚታፈን፣ ሰብሉ በማሳው የሚነድበት፣ የሚራብነ የሚጠማ ነው።
ምርጫችን ሁለት ነው። ተናካሽ ውሻ ሆኖ ማገልገልና እንደነ ንጉሱ ጥላሁን ታዬ ደንደአ ለጂቦች መሰጠት ያለበለዚያም ከህዝብ ጋር ቆሞ ከተማ አፍራሽ፣ ሰላይ፣ ገራፊ፣ ጉቦ አቀባባይ አለመሆን ነው።
ከሀምሳ የማይበልጡ የኦፒዲኦ መሪዎች ብርሀን ይሁን ሲሉ የምናበራ፣ ከተማ ይውደም ሲሉ የምናወድም ከሆነ ከፍርድም ከጸጸትም አንድንም።
እነ ሉሉ በመጨረሻው የት ነበርኩ አሉ። ገበሬ በበሬው ያርስበትና ሲያረጅበት እርዶ ይበላዋል። ክፋት ዞሮ ዞሮ ተመልሶ ይመጣል። ዳንኤል በውሾቹ አፍ ከሚኒሊክ በፊት የነበሩትን ክፉ ገዢ ያስታውሳል። በመጨረሻው እኚህ ጨካኝ ገዢ የግፍ ቀሚስ አልብሰው አቃጠሏቸው። አንድ ገጣሚ ይህንን አለች።
“አንተ ክፏ ነበርክ ክፏ ሰደደብህ
እንደ ገና ዳቦ እሳት ሰደደብህ” አለች።
የብልጽግና ጨካኞች መጨረሻው እንዲህ እንዳይሆን።
The opinion expressed in this article is that of the author