“አምሓራውን ምን በላው?” ብአዴንንስ ማን ወለደው?

ራሴላስ ወልደማርያም

አምሓራ በኢትዮጵያ ረጂም ታሪክ ውስጥ ብዙ አኩሪ ታሪክ ያለው ብልህና አስተዋይ ሕዝብ ነበር። ለነጻነቱ ለመብቱ የሚሞት፣ ከሆዱ ነጻነቱን የሚያስቀድም፣ ለማንም ሎሌና ባርያ ከመሆን ሞቱን የሚመርጥ ኩሩ ህዝብ ነበር። አሁን ብአዴንን ማን ወለደ? ማንስ ከለሰው ? ለምን እንዲህ ጉራማይሌ ሆነ?

ንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ነፍሳቸውን ይማርና ““አም” ማለት በግዕዙ “ህዝብ” ሲሆን “ሓራ” ደግሞ ነጻ ማለት ነው ብለው ጽፈው አልፈዋል። ለምሳሌ “ሓርነት ግንባር” ማለት የነጻነት ግንባር እንደሚባለው ማለት ነው። “አም’ሓራ” ማለት እንግዲህ “ነጻ ህዝብ” ማለት ነው። ማንም ነጻ ሰው “አምሓራ” ይባላል።

ባለፉት 36 ዓመታት ግን ነጻ መሆኑን ትቶ ባርነትን የሚሻ፣ ወንድሙን በመሰለል፣ በማስገደል እንደ ውሻ አጥንት እንዲጣልለት ጭራውን የሚቆላ አማራ ተባዝቶ ተበትኗል።

ዛሬ ለ10 ሺ ብር ደሞዝ ኢንሳና ደህንነት ተቀጥሮ የወንድመን ስልክ የሚጠልፍ፣ ለሶስት ሺ ብር ደሞዝ ደግሞ ወታደር ተብሎ ራሱ ላይ የሚተኩስ፣ የእናቱን ገበና የሚሸጥ። በፊት አማራነት በትውልድ የሚተላለፍ ይመስለኝ ነበር። አሁን ግን አምሓራነት በትውልድ የሚወረስ ሳይሆን በእድገት፣ በተግባርና በስነምግባር የሚወረስ ይመስላል። ንቡረ እድ ኤርምያስ አንድ ሰው ከማንም ይወለድ፣ ከጋሞም ይምጣ ከገመሚራ “ነጻ ሰው” ከሆነ አምሓራ ይባላል ብለው ነበር። ነጻ ያልሆነ በምንም አይነት “አምሓራ” አይባልም።

እኔ ተዳፈርክ እንዳልባል ይሄንን ሀሳብ ለአንድ አመት በውስጤ ይዤው ቆይቻለሁ። በማስታወሻ ደብተሬ ላይ አምሓራን ምን በላው ብዬ ጽፌ ነበር።

የአምሓሮች አመጽ፣ የአድማ በታኝና የባርህር ዳር ጉዞ

የዛሬ 11 ወር፣ ልክ ከፋሲካ በኋላ የአማራ ልዩ ሀይል ትጥቅ ይፍታ የተባለበት ግዜ ነበር። ሰዎችን ለማግኘት በዛውም ለመታዘብ ባህርዳር ሄጄ ነበር። በርካታ የአምሓራ ወጣቶች ልዩ ኃይላችን መፍረስ የለበትም ብለው መንገድ ዘግተው ከመከላከያ እና ከብአዴኖች ጋር ገጥመው ህይወታቸውን እየሰጡ ነበር። ህዝቡ በመላው የአማራ ክልል ግልብጥ ብሎ ልዩ ሀይላችን ትጥቁን ከፈታ ልዩ ኃይልም አምሓራውም ለአደጋ ይጋለጣል ብሎ ነበር ይተናነቅ የነበረው። ይሁንና ባህርዳር ሆኜ ያየሁዋቸው አንዳንድ ሰዎች አምሓራውን ምን በላው እንድል አደረገኝ? በመላው ኡትዮጵያም አማራው ሲታረድ ዝም፣ ቤትህን አፍርስ ሲባል እሺ፣ የነፍ አባቱ ሲታረድ ሻማ የሚያበራ እንጂ የማይንፈራገጥ፣ ተነስ ሲሉት የሚነሳ ሆነ። በኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥር ትልቁ ብሄረሰብ ሆኖ ሳሰል ግብረ መልሱ ግን እንደ አንድ አናሳ ቡድን ነው።

ያኔ 11 ታጣቂዎች እንደ ጆንያ በሚኒባስ ጣራ ላይ ተደራርበው ተጭነው ከባህር ዳር ሲወጡ አየሁ። ከዛ አብሮኝ የነበረውን ጠየቅከት። እነዚህማ ባለፈው ፈርሳችሀል ተብለው የተበተኑት የአማራ ልዩ ሀይሎች ናቸው። አሁን ብአዴኖች ሲጨንቃቸው ወደ ካምፕ ግቡ ብልዋቸው ነው አለኝ። አሁን አምሓራው ለነሱ መብት ብሎ ይሞታል እነሱ ደግሞ ለሽመልስ አብዲሳ የተሀድሶ ስልጠና እየገቡ ነው አለኝ።

ይሄንን ስሰማ አንድ ነገር ከሰውነቴ ውስጥ ሲፈርስ ተሰማኝ። ህዝቡና ወጣቱ ለአማራ ልዩ ኃይል መብት ህይወቱን ሰጥቶ እየሞተላቸው እነሱ ደግሞ የሽመልስ አብዲሳንና የአብይ አህመድን ትእዛዝ ተቀብለው ጠመንጃቸውን ለማስረከብ ነው መኪና እንኳን አቅርቡልን ሳይሉ በሚኒባስ ጣራ ላይ ተጭነው የሚሄዱት ብዬ አዘንኩኝ። በዛ ሳምንት ደግሞ በጣም የማከብረው የሞቀ ስራውንና ትቶ ለአምሓራው መብት ሊታገል ወደ አምሓራ ክልል የመጣ ሰው እነ ዶ/ር ይልቃል ከፍያለና ደሳለኝ ጣሰው አፍነው ይዘው ለኦፒዲኦ ሰጡት በተባለበት ሳምንት ነበር።
ከዛ ማስታወሻዬን አውጥቼ በተሰበረ ልብ “አምሓራውን ምን በላው?” ብዬ ጻፍኩኝ። ይህ ጽሁፍ የዚህ ርዕስ ሆነ።

አምሓራ

ይህ አምሓራ /ነጻ ህዝብ/ ብለው ሌሎች ስም የሰጡት፣ የነ ጣይቱ ብጡል፣ የነ ምኒሊክ፣ የነ ቴዎድሮስ፣ የነ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ የነ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ፣ የነ ቴዎድሮስ ፣ የነ ፋሲለደስ፣ የነ አበበ አረጋይ ብልህነት የት ገባ? እንዴትስ ልጅ መውለድ አቃታቸው ብዬ አሰብኩ? ታድያ የነዚህ ብልሆች የልጅ ልጆች ምን በላቸው? ዘር አልተኩም ማለት ነው?

እንዴት ከሁሉ ብሄር በታች ይህንን ተንኮል እንኳን መረዳት የሚያስችል ህሊና ያጡ ሰዎች በአማራው ውስጥ በዙ አልኩኝ? እዚህ ክፍለ ሀገር፣ በላይ ዘለቀ በተዋደቀበት ምድር እነ በረከት ስምዖን እንኮኮ ተብለው ክቡርነትዎ እየተባሉ ኖረው ሄዱ። አሁን ደግሞ የራሱ ልጆች ታግለው አሸንፈው የሚያርዱትን እነ ሽመልስ አብዲሳን ጃኖ የሚያለብስ ተንበርክኮ ተፈናጠጥብኝ የሚሉትን አማሮች ማን ወለዳቸው? እንዴት ለውርደትና ለእርድ እየተጠራ መሆኑን መረዳት የሚያስችል ህሊና ያጣ አማራ ተፈጠረ አልኩኝ?

ህዝብ ለልዩ ሀይሉ ብሎ እየተናነቀና እየሞተ እያለ እንዴት ለራሳቸው መብት ለመታገል ቢያቅታቸው እንዴት ከገዳያቸው ጋር ለመተባበር መረጡ አልኩኝ። ለምንስ አድማ በታኝ፣ እና ሚሊሽያ ሆኑ? እነዚህ አምሓራ ይባላሉን?

ደግሜ ደጋግሜ እንዴትስ እንዲህ ማሰብ የማይችል አማራ በአምሓራ ውስጥ ተፈጠረ አልኩኝ? እንዴትስ ለራሱ ነጻነት ወንድሙ ሲሞት እሱ ለራሱ ሰጻነት መሞት ቢያቅተው ለሱ ነጻነት የሚታገለውን ወንድሙን ለመግደል ቃታ የሚስበው ጋር ይተባበራል አልኩ? ቁጭ ብዬ ማልቀስ አማረኝ።

ፕሪቶርያና አማራ

የፕረቶርያ ስምምነት ብለው አማራውን ትጥቅ አስፈትተው፣ ራያንና፣ ጠገዴን፣ ሁመራን ለህወሀት ሰጥተው አማራውን ማዋረድና ማስጨፍጨፍ ነው አላማቸው። ታድያ ይሄንን እንዴት እነ ደመቀ መኮንን፣ ዶ/ር ይልቃል ከፍያለ፣ እነ ተመስገን ጥሩነህ፣ እነ አገኘው ተሻገር፣ እነ አረጋ ከበደ፣ እነ ደሳለኝ ጣስው መረዳት አቃታቸው። እንዴትስ እራሳቸውን ቤተሰባቸውን የሚከላከሉበትን ጠመንጃ አስረክቡና ተሰልፋችሁ ታረዱ ይላሉ የሚል ሙግት በውስጤ መጣ። ቅስሜ ተሰበረ። በእርግጥ “አም’ሓራ” ጠፍቶ አማራ ተራባ አልኩኝ? በአምሓራ ወጣቶች ትግልና ትንቅንቅ ብኮራም፣ በህወሓትና ኦፒዲኦ አማሮች አዘንኩኝ። ማንም ሳላናገር ወደ ሆቴሌ ተመልሼ ሻንጣዬን ይዤ ባህርዳርን ለቀቅኩ።

ይሄንን ስሜት በውስጤ የተቀበረውን ለማንም አልተናገርኩም። በግል ማስታወሻዬ ላይ “አማራውን ምን በላው?” ብዬ የጻፍኩት ዛሬም ማስታወሻዬን ሳገላብጥ አያታለሁ።

የህወሓት አማሮች

ለመሆኑ ያ ነጻ ህዝብ አምሓራ ተብሎ የተጠራው የኢትዮጵያ መስራች ህዝብ የት ገባ? የተባለውን ቀርቶ የታሰበውን የሚረዳ ብልህና ኩሩ ህዝብ እንዴት እንደ ዶ/ር ይልቃል ከፍያለ? ጀነራል አበባው ታደሰ፣ ደመቀ መኮንን፣ አገኘው ተሻገር፣ ሰማ ጥሩነህ፣ በለጠ ሞላ፣ ዳንኤል ክብረት፣ አረጋ ከበደ፣ ደሳለኝ ጣሰው፣ ጄኔራል መሀመድ ተሰማ፣ አቶ አብዱ ሁሴን፣ አቶ አህመዲን መሀመድ፣ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ፣ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ፣ ዶ/ር በጋሻው አወቀ፣ አቶ ብርሀኑ ጎሽም፣ ዶ/ር ሰቡህ ገበያው፣ አቶ ክብረት አህመድ፣ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ፣ ዶ/ር ደመቀ ቦሩ ከማን ዘረመል ተፈጠሩ አልኩኝ?
እንዴት ለራሱ መብት የሚታገልለትን ወንድሙን ይሰልላል፣ ይገላል? በወለጋ በአርሲ እያሰለፈ ምንም ሀጥያት የሌባቸውን ህጻናት፣ እናቶች፣ መነኩሴዎችና ሼኮች የሚያርድ ሀይል ትጥቅ ፍቱልኝና አሰልፌ ልረዳችሁ ሲል እሺ ይባላል? እናታቸውን የሚያሳርዱ፣ እህታቸውን የሚያስደፍሩ ከየት መጡ?

ሳይገባቸው ሳያዩ ቀርተው ይሆን አልኩኝ? ከወለጋ ዩኒቨርስቲ 17 ልጃገረዶች ተጠልፈው ሲወሰዱ ንጉሱ ጥላሁን እያወቀ ለምን ለነሽመልስ አብዲሳና እና የጃን መሮ ገጽታ ግንባታ ዋሸ? እውነቱን መናገሩ ለአለቆቹም መፍትሄ እንዲሹ፣ ራሱም እንዲከበር፣ ለልጆቹም ቤተሰቦች እርማቸውን እንዲያወጡ ይረዳ ነበር። ይሁንና የጃል ማሮና ጭካኔና ለአብይ መሰሪነት ለመሸፋፈን ዋሸ። አሁን ንጉሱ ጥላሁን የት ነው ያለው? እስር ቤት።

አብይ አህመድ እንኳን ለአማራ ወዶ ገብ ስልጣኑን ለለቀቀለት ለለማ መገርሳ አልራራም። ቄሮን ቀስቅሶ ለስልጣን ላበቃው ለጃዋር አህመድ ያልራራ ለወዶ ገብ ለአበባው ታደሰ ይተኛል? ከአብንና ከጃዋር ጋር ሲተናነቅለት ለነበረው ታዬ ደንደአ ያልተኛ ለወዶ ገብ ሎሌ ጀነራል መሀመድ ተሰማ ይመለሳል?

እነዚህን ሰዎች ሳይ ነው እንዲህ አይነት ሎሌዎች በአማራ ዘረመል ተፈጠሩ የምለው?

ታዛዥ ብሆንለት አጥንት ይጥልልኛል ብለው የሚያስቡ ውሾች ለምን በአማራ ማህጸን ተፈጠሩ። ለምንስ በዙ?።

በወለጋ “ወላሂ ሁለተኛ አምሀራ አልሆንም” ካለችው ልጅ የዳንኤል ክብረት ሀጥያት በላይ ሆኖ ይሆን? ስንት ዳንኤል ክብረት ከኦሮሙማ ፍርድ ያመልጣል?

እንዴት እነ እነ አረጋ ከበደ ከነዶ/ር ይልቃል ከፍያለ ስህተት መማር አቃታቸው? ለአማራው ህዝብ እኩልነትና ነጻነት ብለው የሸፈቱትን የአማራ ልጆች እያነቁ በመስጠት በሽመልስ አብዲሳ ለመወደድ የሚመርጡ ሆኑ? አሁን የዶ/ር ይልቃል ህይወት እሱ ፈቅዶ አንቆ አሳልፎ ከሰጣቸው በታች ነው? እነሱ በህግ እስረኞች እሱ ደግሞ የግል እስረኛ ነው? እነሱ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ለአማራው ይዘምራሉ፣ እሱ ግን እንደ ሸለምጥማጥ የተቆፈረለት ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ ይውላል።

የዛሬ ሁለት አመት ከአበባው ታደሰ ጋር ጎንደር ጥምቀት ላይ ነጭ ለብሶ በህዝብ ታጅቦ ሰው እጅ ሲነሳ የነበረ የትልቁ ብሄረሰብ መሪ ዶ/ር ይልቃል ከፍያለ እራሱን ዝቅ አድርጎ ለሽመልስ አብዲሳና ጃል ማሮ አገልጋይ ልሁን በማለቱ ተዋረደ። የአበባውም፣ የአረጋ ከበደም፣ የደሳለኝ ጣሰውም የሳህለወርቅ ዘውዴም እጣ ፈንታ ከዶ/ር ይልቃል ከፍያለ የባሰ ነው።

በአማራና በአምሓራነት መሀከል ያለው ልዩነት ተለይቶ ነጥሮ መውጣት አለበት። እንደነ ናሁሰናይ ያለ አምሓራ እንዳለ ሁሉ እነ አረጋ ከበደም ተወልደዋል።

ለኔ ይልቃል ከፍያለ፣ ዳንኤል ክብረት፣ ደመቀ መኮንን፣ አረጋ ከበደ፣ ደሳለኝ ጣስው፣ ተመስገን ጥሩነህ አምሓሮች አይደሉም። በምርጫው ባሮች ናችው። ለኔ እነ መምህር ፋንታሁን ዋቄ፣ መምህር ዘመድኩን በቀለ፣ ቶሎሳ ኢብሳ፣ ታዬ ቦጋለ፣ ታልዲዎስ ተንቱ፣ ፕሮፌሰር ሀይሌ ላሬቦ፣ ወዲ ሻምበል፣ ኦባንግ ሜቶ፣ ዶ/ር አረጋዊ (የአጋዚያን መሪ) ባርነትን የጣሉ እውነተኞቹ አምሓሮች እነሱ ናቸው።

በጥቅል ገዳዩም ሟቹም፣ ባርነት የመረጠውም ነጻውም ሁሉ ጎጃም ጎንደር፣ ወሎና ሸዋ ስለተወለደ ብቻ አምሓራ አይሆንም። እራሱን ነጻ ያላደረገ አይደለም አም’ሓራ የሚባለው።

ሁሉም በተግባር እኔ አምሓራ ወይስ ባርያ ነኝ ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት። ለምንስ አምሓራ ሆኜ ተወልጄ ባርነትን በተግባር መሻት መረጥኩ ብሎ እራሱን መጠይቅ አለበት? ባርነት ለነ ንጉሱ ጥላሁን፣ ለነደመቀ መኮንን፣ ለዶ/ር ይልቃል ከፍያለ ምን አመጣላቸው? ለህዝባቸው ለወገናቸው ጽምጽ ሆነው ቢሄን ኖሮ ህዝብ መከታ ይሆንላቸው ነበር። የመረጥኳቸው ልጆቼ እነሱ ናቸው አትንኩዋቸው ብሎ ሰልፍ ይወጣ ነበር፣ መንገድ ይዘጋ ነበር። ገዱ አንዳርጋቸው ብአዴን ቢሆንም ኮለኔል ደመቀን አሳልፌ አልሰጥም ስላለ በህወሓት ተፈራና ተከበረ እንጂ አልተዋረደም።

እነ ዶ/ር ይልቃል ከፍያለ ግን ለህዝባቸው ድምጽ ከመሆን ይልቅ ቤትና መኪና ፈልገው የሺንት ቤት ወረቀት መሆን መረጡ? ተጠቅመው አቆሽሸው ጣሏቸው። ነገ የይልቃል ከፍ ያለም የናሁሰናይም ልጆች ያድጋሉ። ታሪካቸው ይጻፋል። ነጻነት ሲመጣ ለጣልያን ያደረና ፓስታ ሹታ የበላ ልጆቹን አዋረደ። ቆሎ ቆርጥመው ጫካ ገብተው ለነጻነታቸው የቆሙት ደግሞ ራስ ተባሉ። ራስ መስፍን ስለሺ፣ ራስ አበበ አረጋይ ልጆቻቸው እስከዛሬ እኔ የእንትና የልጅ፣ልጅ፣ልጅ ነኝ ብለው የመንፈስ ኩራት ይለብሳሉ።

በከተማም በስደትም ለኦሮሙማ ባርያ ለመሆን ትንሽ መሬት ትንሽ አጥንት እንዲጣልላቸው ለነሱ ነጻነት የሚታገሉትን የሚሞቱትን የሚሰልሉ ወሬ የሚያቀርቡ መንፈሰ ባርያዎች ሚሊዮኖች ናቸው። እነዚህ ደግሞ የብአዴን ብልጽግና ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆን በየ ትንንሽ ቢሮ ይገኛሉ። በገቢዎች፣ በክፍለ ከተማ፣ በደህነት ቢሮ፣ በኢንሳ፣ በአድማ ብተና፣ በሰራዊት፣ በኢምግሬሽን ውስጥ ያሉትንም አማራ ይጠቀልላል። እነዚህ ሌቦች አምሓራ መባል የለባችውም።

ዮቲዩቡንም የያዙት እውነትን ተናግረው የአምሓራን ዳግም ውልደት ከማምጣትና ድክመታችንንና ህጸጻችንን እያስወገድን ወደ አምሓራነታችን እንድንመለስ ክመጣር በከንቱ ውዳሴ፣ የተጋነነ ዜና፣ የሚታገለውን ሳይሆን የሚያወራውን በማንገስ የሱ ጭፍራ ለመሆንና አንድ ቀን ፍርፋሪ ለመልቀም የሚመኙትንም ይጨምራል። አምሓራነት ባህርይና ተግባር ነው።

አምሓራነት ያልገባው አምሓራ መሆን አይችልም። እራሱን ነጻ ያላደረገ አማሓራ ነኝ ማለት አይችልም። አምሓራ የነጻ ዜጎች ስብስብ እንጂ የአድርባዮች፣ ለዳረጎት ገዳዮች፣ የሰላዮች፣ ለአድማ በታኞች፣ ለብአዴን አሽቃባጮች፣ ጋዜጠኖች፣ አቃቤ ህጎች፣ ዳኞች መገለጫ አይደለም።

አምሓራ ነኝ የሚል ወንድሙን ሰልሎ፣ አስገድሎ፣ እህትቱን አስደፍሮ ቁራሽ መሬት፣ የመንግስት መኪና፣ የመንግስት ቪላ ውስጥ መኖር የሚመኝ አይደለም።

እነዚህ ችጋራሞች እጣ ፈንታቸው የነ ንጉሱ ጥላሁን ነው። መዋረድ ነው። እስቲ ንጉሱ ጥላሁንን ጌታቸው ረዳን እናወዳዳድር። ጌታቸው አብይን ቆዳው እንዳይሸጥ አድርጎ ሲሰድብ ነበር ይሁንና ደጋፊ (Constituency) አለው። ደጋፊው አሳልፎ ስላልስጠው ተከብሮ ከአብይ አጠገብ ተቀምጦ ንግግር ያደርጋል። ቤተመንግስት ሲገባ አብይ ጫፌን አይነካኝም ደጋፊ አለኝ፣ ደጋፊዎች ይጮሁልኛል፣ ከከፋም ይዋጉልኛል ብሎ በልቡ ያምናል። የአብይ ባለሟል የነበረው ንጉሱ ጥላሁን ግን ከወለጋ ተወስደው ግፍ የተፈጸመባቸውን ልጃገረዶች ድምጽ ከመሆን ለኦነግ ሸኔ አሽከር ለመሆን ዋሸ። አሁን ሲታስር እንደ ታዬ ደንደአ ለዜና አልብቃም።

የራያ ዳግም ወረራ

አሁን ደግሞ አረጋ ከበደ እና ደሳለኝ ጣሰው ታዘው መቀሌ ተልከው እነ ጌታቸው እንዲያስፈራሩዋቸው ተደርገው ራያን ሰጥተው አስተዳደር አፍርሰው ለህወሓት አስረክበው መጡ። ነገ ደግሞ ከጠገዴ፣ ከሁመራ ህዝብ አፈናቅለው አስወጥተው ይሰጣሉ። ከዛ ደግሞ ወሎ እኮ ኦሮሞ ነበር ብለው ፈርመው ያፈናቅላሉ። እነዚህ በክፍለ ሀገር በመወለዳቸው ብቻ “አምሓራ” መሆን ይችላሉ?

ወገኔ ንቃ። ዝም ብለህ ጭራህን እየቆላህ አትጥፋ። የነ ኦሮሙማ አላማ ከአዲስ አበባ፣ ከመላው ኢትዮጵያ፣ ከጎጃም ነቅለው መንዝ ተራራ ላይ ተንጠልጥለህ የኦሮሙማ ባለ ጸጋ ልጆች ቱሪስት እያመጡ እንደ ሙርሲ ያስጎበኙታል አቅደዋል።

ይህ እቅድ በጽሁፍም በቃልም ተነግሮሀል ስለዚህ አማራ ነኝ ብለህ የምትመጻደቅ መጀመሪያ እኔ በእውነት አምሓራ ነኝን በል። የባሪያ የይሁዳ ህሊና ይዘህ ወንድምህን እየሸጥክ አምሓራ ነኝ አትበል። ከዛሬ ጀምሮ እኔ አምሓራ ነኝ ወንድሜን ገድዬ፣ ሰልዬ፣ አፈናቅዬ፣ ወታደር፣ አድማ በታኝ፣ ፌዴራል ፓሊስ ሆኜ ወገኔን ፈጅቼ መጨረሻ እኔም ከምፈጅ ከዛሬ ጀምሮ እኔ ባርያ ሳልሆን አምሓራ ነኝ በል። የራስህን ሽክም እራስህ ተሸከም፣ የራስህን ነጻነት እውጅ፣ ማስመሰሉን ትተህ አምሓራ ሁን።

ባለ ፒኤችዲም፣ ፕሮፌሰርም ጠቢብም የተባልከው ምናለ ለነጻነትህ ለመብትህ የሚታገሉልህን ባትረዳ እንዴት ላንተው መብት የሚታገሉትን አሳልፈህ ትሰጣለህ? ከዛሬ ጀምሮ ነጻ ሰው አምሀራ ሁን። የትም ተወለድ፣ ጋምቤላም ይሁን ጂንካ፣ ጉራጌም ይሁን ወላይታ፣ ትግራይን ይሁን ጅጅጋ እራስህን ነጻ ዜጋ ሁን። በግእዝ “ነጻ ህዝብ” አምሓራ ይባላልና።

የዚህ ጽሁፍ መልእክት

ይህ ትግል የብሄረተኝነት ትግል አይደለም ነጻ ዜጋ የመፍጠር እንጂ። ተገዢ ባርያ በመሆን ምንም አይተረፍም። ስለዚህ ሁላችንም አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሀድያ ጉራጌ ስንል በመጀመሪያ እኔ ነጻ ዜጋ ነኝ ወይስ ባርያ እንበል። ከዛ ነጻ አውጪ ስንት ብቅ የራሳችንን ነጻነት እናውጅ። ነጻ ዜጎች ናቸው ነጻ ሀገር መመስረት የሚችሉት። የስነልቦና ባሮች ይሸጣሉ ይለወጣሉ ጌታቸው ይቀያየራል እንጂ ህይወታቸው አይቀየርም። እኛም እራሳችንን ባሮች ስላደረግን ከደርግ ወያኔ፣ ከወያኔ፣ ኦነግ፣ ነገ ደግሞ ኦነግ ሸኔ ነው የሚሸጠን የሚለውጠን። ስለዚህ ነጻነታችንን እናውጅ። እኛ ነጻ ዜጋ የሆንን ማግስት ሀገራችን የኛ የነጻዎቹ ትሆናለች።

ነጻነት ያለ ዋጋ አይመጣም። እኛ 120 ሚሊዮን ነን። አሳዳሪዎቻችን ግን አንድ መቶ አይሆኑም። ግን እንደ ጎልያድ ገዝፈው እንድናያቸው ይሰራሉ። ስለዚህ እኛ እንደጉንዳን በትንሹ በየቀኑ ከቆነጠጥን አንበሳ ይሁን ነብር በሰፈራችን አይደርስም።እንደ ምስጥ ትናንሽ ማይክሮ ግራም ሁላችንም ከቆነጠርን ግንዱን በልተን እንጨርሰዋለን። ስለዚህ እስቲ ከእንቅልፋችን ስንነሳ አንዲት ትንሽ ነገር እናድርግ። ለምሳሌ አንድ ለስርአቱ አገልጋይ የሆነ ወንድም ወይንም ጓደኛ ካለን ጠርተን እባክህ ወንድሜ በወገንህ ላይ አትጨክን እንበለው። ለ30 ዶላር በወር ደሞዝ ወንድምህን አትግደል ተው እንበለው። ለሚታገለው ሽክሙን እናቅልለት። እናበረታታው። ይህ ነው ነጻ ሀገር የሚፈጥረው። ነጻ ሳንሆን ነጻ ሀገር መፍጠር አይቻልም፣ ልድገመው አይቻልም።

 

 

ጽሁፉ የሚያንጸባርቀው የጸሃፊውን ሃሳብ ብቻ ነው።