ከአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ-አምሐራ) የተሰጠ የአንድነት መግለጫ

ከአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ-አምሓራ) የተሰጠ የአንድነት መግለጫ!

የኢትዮጵያ ፖለቲካና ሃገረ መንግስት ዶክትሪን የተመሰረተበት መሰረትና የቆመበት አምድ አማራ ጠልነትን ማዕከል በማድረግ መሆኑ ለሁሉም አማራና የአማራን ህዝብ ሁለንተናዊ መከራና የዘር ጥፋት ለሚከታተል ኢትዮጵያዊ ሁሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው:: አማራ ጠልነት የሃይል ማሰባሰቢያ የድርጅት መመስረቻና ማቋቋሚያ የመንግስት ስርዓት መገንቢያ የህገ መንግስት ማርቀቂያና ማስፈፀሚያ እንዲሁም የስልጣን መውጫና የስልጣን ማራዘሚያ የፖለቲካ መሳሪያና ርዕዮተ አለም ከሆነ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ አስቆጥሯል::

በመሆኑም የሃሰት ትርክት የወለደዉን አማራ ጠልነትና ተያይዞ በህዝባችን ላይ የብልፅግናው መንግስት እየፈፀመበት ያለዉን የዘር ማጥፋትና የዘር ማፅዳት ለመከላከልና ለመቀልበስ የአማራ ፋኖ ይፋዊ የፖለቲካ የትጥቅ ትግል ዉስጥ መግባቱ ይታወቃል:: ምንም እንኳ የአማራ ፋኖ በራሱ ነፃ ፈቃድ በራሱ ትጥቅና በራሱ ስንቅ ወደ ትግል ሜዳ የገባ ቢሆንም በአንድ ርዕዮትና በአንድ ድርጅት ለመስራት ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ገጥመዉታል::

የመጀመሪያው ችግር ታጋዩን የትግል መስመሩን ድርጅትና የመተዳደሪያ ህግን ባግባቡ ቀርፆና ሰርቶ ለመምጣት ጊዜና ተፈጥሯዊ ትግሉ የሚፈልገው እድገት የያዘው ሲሆን ሁለተኛው ችግር የግለሰቦች ፍላጎትና የምኞት ርዕዮት በመካከሉ መሰንቀሩ ነው::

ትግላችንን በድል ለማጠናቀቅ ወጥ በሆነ የትግል መስመር ዉስጥ የሆነ ታጋይን መፍጠር፣ በድርጅት አካልነት ህያው የሚሆን የትግል መስመር፣ እንዲሁም በህግ የሚጠየቅና የሚጠበቅ ታጋይ፣ የትግል መስመርና ድርጅት በእጅጉ አስፈላጊ ነው::
ታጋይ የሌለበት የትግል መስመር፣ የትግል መስመር የሌለው ድርጅት፣ ድርጅት የሌለው ገዢ ህግ፣ ፍጡር አልባ ፈጣሪ ሲመስል፧ ህግ አልባ ድርጅት፣ ድርጅት አልባ የትግል መስመር፣ እንዲሁም የትግል መስመር የሌለው ታጋይ፣ ፈጣሪ አልባ ፍጡርን ይመስላል::

የአማራን ህዝብ ከተቃጣበት ጥፋት ለመታደግ የታጋይ ችግር የለበትም:: ነገር ግን የጠራ የትግል መስመርን ቀርፆ የትግል መስመሩን፣ መንገዱና ርዕዮቱ ያደረገ ድርጅት መፍጠር አለመቻል፣ መሰረታዊ የአማራ ህዝብ ትግል ችግር ሆኗል:: ይህንን ችግር በዋናነት እያባባሰው የመጣው ደግሞ በትግሉ የሚነግዱ የደም ነጋዴዎች መበራከት ነው:: እነዚህን የደም ነጋዴዎች ለማስቆም ደግሞ በክፍለ ሃገር ደረጃም ሆነ ጠቅላላ እንደ አማራ የጠራ አንድ ወጥ የፋኖ አደረጃጀት መዘርጋትና መምራት በእጅጉ አስፈላጊ ነው::

በመሆኑም በወሎ ቤተ-አምሓራ የምንገኝ የፋኖ አደረጃጀቶች በዛሬው ዕለት ማለትም ጥር 14/2017 ዓ.ም በታሪካዊቷ የራስ ወሌ ብጡል ከተማ በሆነችው በመርጦ በመገናኘት አንድነታችንን የሰራንና አንድ ድርጅት የመሰረትን መሆኑን ስናበስራችሁ በታላቅ ደስታ ነው:: ስምምነቱንም የመርጦ ስምምነት (Merto Declaration) ብለነዋል::
ስለሆነም:

1ኛ.በዋርካው ምሬ ወዳጆ የሚመራው በአማራ ፋኖ በወሎ ስር የሚገኙ በአራት ኮር የተደራጁ ክፍለጦሮች ማለትም፣
1.አሳምነው ክፍለጦር
2.ሃውጃኖ ክፍለጦር
3.የጊራናው ባለ ሽርጡ ክፍለጦር
4.ዞብል አምባ ክፍለጦር
5.ካላኮርማ ክፍለጦር
6.ታጠቅ ክፍለጦር
7.ዲቢና ወርቄ ባለ ሽርጡ ብርጌድ
8.አማራ ሳይንት መቅደላ ክፍለጦር
9.ንጉስ ሚካኤል ክፍለጦር
10.ቀኝ አዝማች ይታገሱ አረጋው ክፍለጦር
11.ተፈራ ማሞ ክፍለጦር
12.እሸት ክፍለጦር
13.ሃይሉ ከበደ ክፍለጦር
14.ተከዜ ክፍለጦር
15.ጥራሪ ክፍለጦር
16.ማረጉ ተማረ ክፍለጦር
17.ዉባንተ አባተ ክፍለጦር
2ኛ.በአርበኛ ድርሳን ብርሃኔ የሚመሩትና በሁለት ኮር የተደራጁት
1.ራምቦ ክፍለጦር
2.ራስ አሊ ክፍለጦር
3.የጎፍ ክፍለጦር
4.ቤተ-አምሐራ ክፍለጦር
5.መብረቅ ክፍለጦር
6.ዳግም ክተት ወረኢሉ ክፍለጦር
7.ሸህ ሁሴን ጅብሪል ክፍለጦር
8.ኢንጅነር ደሳለኝ ክፍለጦር
3ኛ.በአርበኛ መቶ አለቃ ዮሴፍ አስማረ የሚመራው ሰርዶ ኮማንዶ ክፍለጦር
በአጠቃላይ ወደ አንድነት በመምጣት ስያሜያችንን “የአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ-አምሐራ)” በሚል የድርጅት ስም የምንጠራ መሆኑን እንገልፃለን:: የድርጅቱን ዝርዝር የአመራር ምደባ በቅርብ ቀን የምናሳውቅ ይሆናል::
ከዚህ ጋር ተያይዞ ለህዝባችንና በአንድነቱ ላልተካተቱ ክፍለጦሮች እንደሚከተለው ጥሪ እናቀርባለን::

  1. የአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ- አምሓራ) በሚንቀሳቀስበት የወሎ ክፍለሃገር ዉስጥ በጉብስላፍቶ ወረዳ በተወሰኑ ቀበሌዎች የሚንቀሳቀሱት የመቅደላ እና የፅናት ክፍለጦሮች በአጭር ጊዜ ዉስት ድርጅታችንን እንድትቀላቀሉ ወንድማዊና ጓዳዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን::
  2. የአማራ ፋኖ የህዝብን አጀንዳ በአግባቡ የተሸከመ እውነተኛ የህዝብ ልጆች የሚመሩት አንድ ወጥ አማራዊ ድርጅት በመመስረት በቅርብ የሚመጣ ስለሆነ ህዝባችን አስፈላጊዉን ድጋፍና ተሳትፎ ማድረጉን እንዲቀጥልና በትግስት እንዲጠብቀን ጥሪ እናቀርባለን::
  3. በተለያዩ የአለም ክፍሎች የምትገኙ ዲያስፖራ ወገኖቻችንና የትግሉ ደጋፊዎች የአማራ ህዝብ ትግል ከመጀመሪያው ጀምሮ በፅናት ስትደግፉ መቆየታችሁ ይታወቃል:: በመሆኑም አሁንም ያልተገደበና ሁለንተናዊ ድጋፋችሁን እንድትቀጥሉ እናሳስባለን::
  4. የአማራን ህዝብ ትግል በባለቤትነት የምትዘግቡ እና ለአለም ተደራሽ የምታደርጉ የሚዲያ አካላትም በትግሉ ላይ ያላችሁን በጎ ተፅዕኖ እንድታስቀጥሉ እየገለፅን ታጋዩን ከትግል መስመሩ፣ ታጋዩና የትግል መስመሩ የሚመሩበትን አንድ ወጥ የአማራ ፋኖ ድርጅት እንድንፈጥር በፅኑ እንድታግዙን ጥሪ እናቀርባለን::

“ሕልዉናችን በተባበረ ክንዳችን”

የአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ-አምሓራ)
ጥር 14/2017 ዓ.ም