(ኢትዮ ፋኖ) ተመስርቶ በይፋ የትጥቅ ትግሉን በመቀላቀሉ የአማራ ፋኖ በጎጃም ደስታ ይሰማዋል

ከአማራ ፋኖ በጎጃም የተላለፈ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት !!

ዛሬ ጥር 20 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፋኖ በደቡብ
(ኢትዮ ፋኖ) ተመስርቶ በይፋ የትጥቅ ትግሉን በመቀላቀሉ የአማራ ፋኖ በጎጃም ደስታ ይሰማዋል ።

የፋኖ ትግል አማራን ህልው ከማድረግ አልፎ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስርዓት ወደ ፍፁም ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊነት የሚቀዬር ዕውነተኛ የትግል መንገድ የሆነ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚኖርባት ሐገር እንድትሆን ያለመ፤ አሳዳጅ እና ተሳዳጅነትን፤ገዳይና ሟችነትን፤ አፈናቃይ እና ተፈናቃይነትን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር እስከወዲያኛው የሚያስወግድበት ነው።
በመሆኑም የአማራ ህዝብ እያደረገው ያለውን አማራን እና ኢትዮጵያን ከዚህ ጨፍጫፊ ስርዓት ነፃ የማድረግ ፋኗዊ የነፃነት ተጋድሎ በውል ተገንዝባችሁ የዚህ ታሪካዊ ትግል አካል እና የዚህ ዘመን የነፃነት ተምሳሌት በመሆናችሁ የተሰማንን ደስታ ለመግለጽ እንወዳለን።

ስለዚህ የኢትዮጵያ ፋኖ በደቡብ ( ኢትዮ ፋኖ ) ይህንን ጣዕረ ሞት ላይ ያለ ስርዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ አስወግደን ለምንመሰርተው እውነተኛ ኢትዮጵያዊ መንግስት ለምታደርጉት ተጋድሎ ያለንን ጓዳዊ ክብር እና ደስታ እየገለፅን :-

  1. በደቡቡ የሐገራችን ኢትዮጵያ ክፍል የምትገኙ ጀግኖች የጉራጌ ልጆች፣ ጀግኖች የሐድያ ልጆች፣ ጀግኖች የሲዳማ ልጆች፣ ጀግኖች የወላይታ ልጆች፣ ጀግኖች የጋሞ ልጆች፣ ጀግኖች የከምባታ ልጆች እና ሌሎች በስም ያልተጠቀሳችሁ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላችሁ ሐገር ወዳድ ወገኖቻችን ይህንን የትጥቅ ትግል እንድትቀላቀሉ እንጠይቃለን።
  2. የአፋር፣ የሶማሌ፣ የጋምቤላ፣ የኦሮሞ፣ የጉሙዝ፣ የትግሬ ልጆች ይህንን ስርዓት ለመጣል በሚደረገው ተጋድሎ ህዝባዊ መሰረት የያዘ አደረጃጀት በመፍጠር ከአማራ ፋኖ ጎን እንድትሰለፉ ስንል ጥሪ እናደርጋለን ።
  3. በየትኛውም የሐገሪቱ አካባቢዎች የምትገኙ ሐገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አሁን ላይ የአማራ ፋኖ የሚያደርገውን የህልውና የነፃነት ተጋድሎ በቻላችሁት ነገር ሁሉ በመደገፍ እኩልነት፣ ፍትህ እና ነፃነት የሰፈነባት ሐገር እንድትኖረን ለማድረግ እና ሐገራዊ የሆነ ጤናማ የፖለቲካ ስርዓት በጋራ እንገነባ ዘንድ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ እንድታደርጉ ስንል ጥሪ እናቀርባለን።
  4. የዚህ ዘመን ፋኖነት ተፈጥሯዊውን የነፃነት ተጋድሎ ወደ ፖለቲካዊ ግብ የቀየርንበት አይነተኛው ከህልውና አደጋ የመውጫ መንገድ በመሆኑ የምናደርገውን የነፃነት ተጋድሎ በልኩ እና የሚከፈለውን ውድ የሆነውን የህይወት ዋጋ ከግምት ያስገባ ብሔራዊ ክብር እንድትሰጡ ለሁሉም ሐገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እና አንቂዎች ለማሳሰብ እንወዳለን።
  5. የአሜሪካ መንግስት፣ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት (ተመድ)፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ህብረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአማራ ህዝብ እያደረገው ያለውን የህልውና ተጋድሎ ቀስ በቀስ ሌሎች ሐገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እየተቀላቀሉት በመሆኑ የዚህን ትጋድሎ ግዝፈት፣ ሐገራዊ እና ፖለቲካዊ ትርጉም በልኩ እና መሬት ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መዝናችሁ እንትረዱት ስንል እናሳስባለን ።

በመጨረሻም ይህ ትግል አማራን እንደ ህዝብ ህልው ከማድረግ እና የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ስርዓት ወደ ፍፁም ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚቀይር ከመሆን አልፎ በቀጠናው ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት መልክ የሚያስይዝ ስለሆነ እና ይህ ትግል የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ የኢትዮጵያ ፋኖ በደቡብ (ኢትዮ ፋኖ) ይህንን ትግል በመቀላቀሉ ለመስራች አባላቱ እና ለማህበረሰቡ ያለንን አድናቆት እና ክብር በድጋሜ ለመግለጽ እንወዳለን።

አዲስ ትውልድ!
አዲስ አስተሳሰብ!
አዲስ ተስፋ!