መልዕክታችን ይድረስ (ከቃሊቲ/ቂሊንጦ ማጎሪያ ቤት)

መላዉ የአማራ ህዝብ እንደሚያዉቀዉ ህዝባችን እየደረሰበት ያለዉን ፈርጀ ብዙ መንግስታዊ በደል ተገንዝበን በደለኛዉን የብልፅግና መንግስት በመታገላችን በየእስር ቤቱ እንገኛለን፡፡

ግፈኛዉ የኦሮሞ ብልፅግና መራሽ መንግስት እኛ በታሰርንለት እዉነት ፊት ቆሞ ለጥያቄዎቻችን መልስ መስጠት ስለማይችል በአፈሙዙ አስገዳጅነት ከያለንበት ለቃቅሞ ማሰርን መርጧል፡፡ይህ መንግስት የመጠየቅ መብታችንን ወንጀል አድርጎ ከሶን በድራማ መሰል ፍርድ ቤቶቹ እያመላለሰን ይገኛል፡፡

ይህ ሁሉ የሚደርስብን የብልፅግና መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ እያደረሰዉ ያለዉን በደል ጠንቅቀን የምንረዳ በመሆኑ ለ “convince and confuse” የአመራር ዘይቤዉ ምቹ ሆነን መገኘት ስላልቻልን ነዉ፡፡ እንዲህ ጠንቅቀን የምናዉቀዉን መንግስት ልናምነዉ አንችልም፡፡ ስለሆነም ከዚህ መንግስት ጋር ያዉም ከህዝባችን በስተጀርባ ልንደራደር አንችልም፡፡

ይህ የማይታሰብ ነገር ነዉ!!! እኛ የምንታገልለትን የአማራ ህዝብ በእጅጉ የምናከብር ዜጎች ነን፡፡ ስለሆነም ይህ ታላቅ ህዝብ ተደራደሩልኝ ብሎ ዉክልና ስጥቶ ሳይልከን ብድግ ብለን ለድርድር የመቀመጥ ድፍረትም ዕብሪትም የለንም፡፡ሃገር የሚመራዉ በማታለልና በማደናገር እንደሆነ ኮራ ብሎ በአደባባይ ከሚናገር መንግስት ጋር ቀርቶ ከተሻለ መንግስት ጋር ቢሆንም በህዝብ ስም ለመደራደር ከህዝብ መወከል እንደሚያስፈልግ በዉል እንረዳለን፡፡

ስለሆነም ከብልፅግና መንግስት ጋር ከህዝባችን በስተጀርባ የምናደርገዉ ቀርቶ የምናስበዉ ድርድር የለም፡፡ በግፍ ታስረን የምንገኘዉም የህዝባችንን ጥያቄ በዋዛ አስማምተን የምንሸጥ ሰዎች እንዳልሆንን የብልፅግናዉ መንግስት ጠንቅቆ ስለሚረዳ ነዉ፡፡ ማንኛዉንም መስዋዕትነት ልንከፍልለት አምነን ለተሰለፍንለት አላማ እስከመጨረሻዉ ታምነን እንደምንቀጥል እና ከህዝብ በስተጀርባ ከግፈኛ መንግስት ጋር የምናደርገዉ አንዳች ድርድር እንደሌለ ለህዝባችን አበክረን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ ህዝባችን ይህን ተረድቶ ከተለያዩ ቦታዎች ከሚናፈሱ መሰረተ ቢስ ወሬዎች እንዳይወዛገብ አደራ እንላለን፡፡

ድል ለአማራ ህዝብ!

ዶ/ር ወንደሰን አሰፋ፣ ጋዜጠኛ መስከረም አበራ እና በዚህ መዝገብ የተከሰሱ ሌሎች የፖለቲካ/የግፍ እስረኞች ከ ቃሊቲ/ቂሊንጦ ማጎሪያ ቤት

 

Letter from Kaliti prison