ከአማራ ፋኖ የጎንደር ዕዝ ምስረታ አስተባባሪ ኮሚቴ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
ለተከበርከው የኢትዮጵያ ህዝብ
ለተከበርከው የአማራ ህዝብ
ለተከበርከው የጎንደር ህዝብ
የአማራ ህዝብ በታሪኩ አይቶት በማያውቅ ሁኔታ የገጠመውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ሁሉን አቀፍ ትግሉን አጠናክሮ ቀጥሏል። በአሁኑ ሰዓት ትግሉ በከፍተኛ ሁኔታ በአይተኬ ውድ የአማራ ልጆች መስዋትነት በአሸናፊነት የትግል ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ምንም እንኳ ጠላት በአገር ሀብት፣ በሙሉ ጉልበትና አቅሙ አማራን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ሁሉንም አይነት ዘመቻ የከፈተብን ቢሆንም በየዘመናቱ ያጋጠሙትን የውስጥና የውጭ ወራሪዎችን አከርካሪ በመስበር የሚታወቀው ጀግናው የአማራ ሕዝብ ለጠላቱ የማይወረወር የብረት አለሎ፣ የማይቆረጠም የድንጋይ ቆሎ ሆኖበታል። በዚህም የአማራ ጠላቶች የሚይዙትና የሚጨብጡትን አጥተዋል።
ተጠናክሮ በቀጠለው የአማራ ሕዝብ የህልውና ተጋድሎ የውስጥ ባንዳዎች እረፍት አጥተዋል፣ በአጭር ጊዜ አማራን አንበረክካለሁ ብሎ የገባው የብልፅግና ወራሪ አገዛዝ የሚይዘው የሚጨብጠው አጥቶ ግራ ተጋብቷል።
አጠቃላይ አገዛዙ መዋቅሩ የፈረሰበት ፣ እግረኛ ሠራዊቱ የአማራን ህዝብ ተጋድሎ መቋቋም ያቃተበት በምናደርሰው ጥቃት እየተበታተነ ያለ ኃይል ሲሆን ጠላት በከባድ የጦር መሳሪያ ፣ በድሮን ቴክኖሎጅ እና በአየር ኃይል ላይ ተመስርቶ ህዝባችን በጅምላ እየጨፈጨፈ ቢሆንም ሕዝብን ታግሎ ያሸነፈ አገዛዝ የለምና የጨፍጫፊው አገዛዝ ጀንበር እየጠለቀችበት ትግኛለች!
በአራቱም የአማራ ግዛቶች እንዲሁም በመላው ዓለም በሚገኝ የአማራው ህዝብ የተጀመረው የህልውና ትግል በዓይነቱ የተለየ ከመሆኑም በላይ በካድሬ ጩኽት፣ በሚሊሻ ጋጋታ፣ በከባድ መሳሪያ ፣ በድሮን ቴክኖሎጅ እና በአየር ኃይል ጋጋታ ሊቀለበስ ካለመቻሉም በላይ የህልውና ትግሉ በማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
የዚህ የትግል ምዕራፍ ነፀብራቅ የሆነው የአማራ ፋኖ ባለፉት ሰባት ወራት በሁሉም አካባቢዎች እያካሄደ ያለው ሕዝባዊ አይበገሬነት የህልውና ትግል ነው::
በጦርነቱ በርካታ ድሎች የተመዘገቡ ከመሆኑም በላይ የአማራን ሕዝብ አንድነት በማጠናከር ረገድ እና አደረጃጀቱንም ከታች ወደ ላይ በማጠናከር የህልውና ትግሉ አይተኬ ሚና በመጫዎት ላይ መሆኑን ተመልክተናል።
የአማራ ፋኖ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ሰባት ቀደምት የፋኖ ፋና ወጊ አርበኞችን በአሰመራጭ ኮሚቴነትና በአማካሪነት በማዋቀር የጎንደር ጠቅላይ ግዛት የፋኖ ዕዝ ለመመስረት በርካታ ስራዎችን በመስራት፤ በጉጉት የሚጠበቀውን የጎንደር አማራ ፋኖ ዕዝን ለማብሰር በእጣት የሚቆጠሩ ቀናቶች ይቀሩታል::
ስለሆነም ኮሚቴው ከዚህ የዕዝ ምስረታ ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች ለመላው የአማራ ሕዝብና ለኢትዮጲያ ሕዝብ ማሳዎቅ ይፈልጋል:-
1ኛ. በጎንደር በሁሉም የአማራ ፋኖ አመራሮች እውቅና ከተመረጡት ሰባቱ አስተባባሪና አስመራጭ ኮሚቴው ውጭ በአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጭ የጎንዮሽ አካሄድ፣ የዕዙን የምስረታ ሂደት ለማደናቀፍ የሚሞክር፣ በእኔ አውቅልሃለው በተናጠል የፋኖን አንድነት ለመሸርሸር የሚሞክር፣ መግለጫ የሚሠጥ፣በሚዲያ የሚዘግብ፣ ሻለቃም ይሁን ብርጌድ እንዲሁም ክፍለጦር መስራቻለሁ የሚል አካል ከዚህ መግለጫ በኋላ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ: መላው ህዝባችን ደግሞ ከአስተባባሪ ኮሚቴው ውጭ የሚደረግን ማንኛውም እንቅስቃሴ የጎንደርን ፋኖ እንደማይወክል እውቅና እንዲወስድ እናሳስባለን።
2ኛ. አጠቃላይ የጎንደር ጠቅላይ ግዛት ፋኖን ወደ አንድ ዕዝ ለማምጣት በምናደርገው እንቅስቃሴ አንድነት የአሸናፊነት መውጫ መንገድ መሆኑን ህዝባችን በውል ተረድቶ የተለመደውን የትግል ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና በቅርቡ ይፋ እስከምናደርግ ድረስ በትዕግስትና በአርቆ አሰተዋይነት እንዲጠብቀን እናሳስባለን።
3ኛ. በወሎ፣ በጎጃም እና በሸዋ ጠቅላይ ግዛት አኩሪ ተጋድሎ እያደረጋችሁ ያላችሁ እህት ወንድሞቻችን በጋራ ክንዳችን ይህን ጨፍጫፊ እና አረመኔ አጋዛዝ ታግለን ለማሸነፍ ትግሉን እንደ አንድ አማራ በአንድነት ትግሉን ቅርፅ አሲይዘን የምንመራበት ወሳኝ ምዕራፍ ሰለደረስን እናንተም እየተዘጋጃችሁ እንደሆነ እናውቃለን ስለሆነም ሁላችንም ዕዞቻችን መስርተን በአንድነት በመታገል ለፍፃሜው ድል እንደምንበቃ አርግጠኞች ነን።
4ኛ ከጽሑፍ መግለጫ ባሻገር ኮሚቴው በድምፅ የሰጠውን መግለጫ የሚዲያ ታጋዮቻችን ለህዝባችን እንድታደርሱልን ስንል እንጠይቃለን።
አማራነታችንን በደምና በአጥንት እናፀናለን!
የአማራ ፋኖ ዕዝ በጎንደር አስመራጭ ኮሚቴ
አርበኛ ሻለቃ መሳፍን ተስፉ
አርበኛ ሻለቃ ሰፈር መለስ
አርበኛ ኮማንዳር አረጋ አለባቸው
አርበኛ ሻለቃ እሸቴ ባዬ
አርበኛ ኮማንደር ደስታው ደመላሽ
አርበኛ ሻምበል ገብሩ እና አርበኛ ሻምበል መሰረት አለሙ (በቃለ መጠይቁ ወቅት በግንኙነት ችግር ምክንያት ያልተገኙ በአሰመራጭ ኮሚቴው ሂደት ውሰጥ ግን ያሉ
ጥር 13/2016
ጎንደር
ምንጭ፣ ሙሉጌታ አንበርብር