የኢትዮጵያ ድል ለምን በየጊዜው ይነጠቃል?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ፕሮግራም የመጀመሪያ ገጽ ብናይ “የኢትዮጵያ ሕዝብ በ1966 እና በ1997 ዓ.ም. የተቀዳጀውን ድል ተነጠቀ” ብለው ነው የሚጀምሩት። ይሁንና ይህ የድል ንጥቂያ እንዳይደገምና ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ምን መደረግ እንዳለበት አጥንቶ ያስጠነቀቀ ምሁር ግን የለም።
የፋኖ አንድነት ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የራሱ ግንዛቤና መግባባት ላይ ደርሷል። ዋናው ችግር መንጋውን በማነሳሳትና ብልጭልጭ ተስፋዎችን በመስጠት፥ የተጋጋለውን ስሜት በመጋለብ ሁሌም ብልጣ ብልጦች ሥልጣን ይቆጣጠራሉ። ለዚህ መፍትሄው በመንጋ ጫጫታ ላለመመራት መጠንቀቅን ጠንካራ ሥርዓት ማድረግ ነው። “አሥር ጊዜ መትረህ አንድ ጊዜ ቁረጥ” ብለው የሚመክሩት፣ የችኮላ ሥራ ችግር እንዳለው ለማስገንዘብ ነው።
በፍጥነትና በችኮላ፥ በጥድፊያና በስሜት የሚፈጸሙ ጉዳዮች አሉ። ጊዜ የማይሰጥ እንደ እሳት አደጋ፥ የመሬት ናዳ፥ የውጭ ጠላት ወረራ፥ እንደ ብልጽግና ያለ በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆነ መዋቅር ዘር የሚያጠፋ ጠላት ሲያጋጥም በዘገምተኛ አካሄድ ተጉዞ ከመጥፋት ፈጥኖ መነሳት የተሻለ ይሆናል። ይሁን እንጂ በእንደዚህ ዓይነት ጊዜ በማይሰጡ ጉዳዮች ውስጥ ስንኳ ፍጥነትና ጥድፊያን ከጭፍንነት ማላቀቅና በስሌትና በጥበብ መጓዝ፥ ሽሽትን እንኳ በሚያስመልጥ አቅጣጫ ለማድረግ መረጋጋትና አርቆ ማየትን ይጠይቃል።
ፍጥነት ከስሌት፥ ጥድፍያ ከጥበበኝነት፥ ስሜታዊነት ከአስተውሎት ሳይጣሉ ሩቅ አይቶና አሥሬ መትሮ አንዴ መቁረጥን ማስማማት የሚቻለው በትጋት፥ በዓላማ ላይ በማተኮር፥ ብዙ ሐሳቦችን ተቀብሎ መዝኖና መርጦ፥ አስማምቶና አሻሽሎ በቁርጠኛ አመራር ሥር መተግበርን ይጠይቃል። በርካታ ነባር ኢትዮጵያዊ የአስተዳደርና የፍትሕ ሥርዓቶቻችንን፣ ተዋረዳዊ ግንኙነታችንን፥ የረዥም ታሪክ ውጤት የሆኑ እሴቶቻችንን ንቀን በጭፍን ተጉዘን አዳዲስ ነገሮችን ለመጨበጥ ከሞከርንበት ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድሎች የከሸፉት ስሌትንና ጥበብን፥ አርቆ ማየትንና ዘለቄታዊነትን በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠ፥ በጥቅሉ ስሜትን በመጋለብ የሚመራ ትግል በመሆኑ ነው።
ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት ድል በግርግር ይነጠቃል። ማሰብ ይቀርና በግርግርና በጩኸት ተነድተን ሊያጠፉን የሚፈልጉ ሰዎች እግር ስር ሄደን እንወድቃለን።
እነዚህ ብልጣ ብልጦች የምንፈልገውን ነገር ያጠኑና መልሰው ይነግሩናል። ኢትዮጵያን ለማጥፋት አድፍጦ የነበረው ኦፒዲኦ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን” ስላለ ብቻ ብዙዎች እግሩ ስር ተደፍተዋል። የወደቅንለት ክፍል ጠቅላይ ሆኖ የፈለገውን ሕግ እና የሕግ አፈጻጸም ይደነግጋል፤ የአገሪቱን ኃብት ተቆጣጥሮ እንደ ደርግ፥ እንደ ሕወሐትና ብልጽግና በሕዝቡ ላይ መከራ ያዘንባል። የጅምላ ፍጅት እስከ መፈጸም ይራመዳል። ሕዝብ ደግሞ አዲስ ለቅሶና አዲስ ትግል “ሀ” ብሎ ይጀምራል።
ለምሳሌ ሕወሐትንና ሥርዓቱን ለመገርሰስ ብዙ የታገሉ ታዋቂ ሰዎች በስሜት ተነድተውና በአብይ ተስፋ ሰጭ ንግግሮች ተታልለው አጥፊያቸው እግር ስር ወድቀው ጫማውን ስመው ሕዝቡ እንዲያምነው አድርገውታል። ዋጋ ከፍለው እርሱን ለሥልጣን ያበቁትን ጀግኖች ማመስገንና መንከባከብ የአብይ አህመድ ቀዳሚ ሥራ መሆን ነበረበት። አብይ ግን ደኅንነቱን፥ ጦሩን፥ ገንዘቡንና መዋቅሩን እስኪቆጣጠር ተቅለስልሶ ጉልበት ሲሰማው ሚሊዮኖችን የሚገድልና አገር የሚያፈርስ አውሬ ሆኖ ተከሰተ። በመጀመሪያ እግሩ ስር የወደቁትንና ታማኝነት ያስገኙለትን ታጋዮች አዋረደ።
ፋኖ እንዲህ ዓይነቱ ግርግር እንዲደገም አይፈቅድም። ፋኖ በሰብአዊነትና ፍትሐዊነት፥ በእውነትና በረዥም የአገር ታሪካዊ መሠረት ላይ ቆሞ አሳታፊና ባሕላዊ የሆነ አደረጃጀት ይዞ የመጣ እንጂ ከላይ ወደ ታች የሚወርድ የኮሚኒስት ድርጅት አይደለም። ባሕላዊ ነው የምንለው፣ ሥልጣን በደም ሳይሆን በተግባር የሚገኝ መሆኑን ታሪክ ስላስተማረን ነው። ኢትዮጵያውያን መሪዎች የሚፈጠሩት በተግባር በሚረጋገጥ ማኅበራዊ ንቅናቄ ነው። ራስ አሉላ አባ ነጋ፣ ፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ፣ ገብርዬ፣ ጃገማ ኬሎና አብዲሳ አጋ የደጃዝማች ወይም የራስ ልጅ ሆነው አይደለም ራስ፣ ደጃዝማች፣ ፊታውራሪ የተባሉት። በትግል ውስጥ ገብተው ጦር ሰብቀው፣ ጎራዴ መዘው፣ ፈረስ ጋልበው፣ ተኩሰው ባሳዩት ጀግንነት እንጂ በድምጽ ብልጫ አይደለም። መሪ በትግል ሜዳ ነው የሚፈጠረው። ብቃት ያለው በትግል ውስጥ መሪ ሆኖ ይመጣል እንጂ ሰባት ኮሚኒስቶች ከውጪ የመሰረቱት እና የመለመሉት ዓይነት ጀሌ በፋኖ ትግል የለም።
ፋኖ “ዲሞክራሲያዊ ነው” የምንለው ከታች ወደ ላይ ስለተገነባ ነው። እንዲሁም በምላስ ጂምናስቲክ የሚገኝ የብልጦች መመረጥ ሳይሆን ራስን ለወገን በመስጠት የሚገኝ መሪነት ነው። ፋኖ፣ ህልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል ያሉ በሰፈራቸው ተሰባስበው ሰልጥነው፣ በገንዘባቸው ታጥቀው፣ የሰፈራቸውን መሪ የመረጡ ብዙ ሺህ ስብስቦች ናቸው።
ፋኖዎች ወኪላቸውን በወረዳ አሰባስበው፣ የወረዳ አመራር ፈጥረው፣ ከዛም የአውራጃና የክፍለ አገር አመራር እየፈጠሩ እንደ ፒራሚድ የጠነከረ ድርጅት መስርተዋል። በቅርብ ቀን ደግሞ የአገራዊ አመራሮቻቸውን ይሰይማሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከመነሻቸው ለሥልጣን አልመው፥ ሤራ ሰንቀው፥ ደጋፊዎችን በኔትዎርክና በእቅድ አፍርተው፥ የፕሮፓጋንዳ ሠራዊት መሥርተው ራሳቸውን ለማንገሥ የሚጋጋጡ የብልጣብልጦችን አመራር ፋኖዎች አይቀበሉም።
ለዚህም ነው ፋኖ ጠንካራና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ተቋም የፈጠረው። አንዱ ለአንዱ ይሞታል እንጂ ወንድሙን አጋልጦ አይሸሽም። ስለዚህ በግርግር የሚፈጠር ከላይ ወደታች የሚሰጥ አመራር የለም። በፋኖነት አጠቃላይ ዕሳቤ ውስጥ ሤራ፥ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አጋጭቶ፣ የተለያየ ቡድን ፈጥሮ ሰውን መካፈልና መምራት የወንድምና የእኅት ደም እንደ መጠጣት ያለ እርም ነው።
ብዙ ጠቃሚ ሥራዎችን የሠሩ ሰዎች የአብይን ንግሥና በስሜት አረጋግጠውና ብዙኃኑን ሕዝብ አሳስተው በማደንዘዝ ለአገር አጥፊው የብልጽግና መሪ ለአብይ አህመድ በማስጎንበስ ስሕተት የሠሩ ታዋቂ ሰዎች ነገሩ የገባቸው፣ ጥፋት የመሥራት አቅም ከፈጠሩለት በኋላ በመሆኑ አፍረው ራሳቸውን ከትግል አግልለዋል።
ሌሎች ደግሞ በጊዜው ጥርጣሬ ያደረባቸው ነበሩ። አብይ አንተ ማነህ? የዚህ ሁሉ መዘዝ ምክንያት የሆነውን ሕገ መንግሥት ታሻሽላለህ ወይ? አዲስ አበባስ የሁላችን ነች ብለህ ታምናለህ ወይ? ብለው የጠየቁ ነበሩ። ይሁንና በመንጋው ተወግዘዋል? ለምን ጠየቅክ? እንዴት ተዳፈርክ? ተብለው ተብጠልጥለዋል፡፡ ለዚህ ጥፋት በከፊልም ቢሆን ተጠያቂዎቹ አብይን ተቀባይነት እንዲያገኝ በችኮላና በስሜት ሕዝቡን ያዘናጉትና ያደነዘዙት በሕዝብ ፊት ክብር የነበራቸው ሰዎች ናቸው።
ይህ እንዲደገም ፋኖ አይፈቅድም። የማይጠየቅ፣ የማይመረመር፣ የማይወቀስ፣ የማይከሰስ፣ ከሕግ በላይ የሆነ መሪ በኢትዮጵያ እንዲፈጠር አይፈቅድም። በፕሮፓጋንዳና በድጋፍ ብዛት፥ በገንዘብና በጥቅማ ጥቅም፥ በመከፋፈልና በማጋጨት ራሱን መሪ ለማድረግ የሚሞክር ሁሉ የአማራ ሕዝብ ጠላት፥ የኢትዮጵያ ሕልውና እንቅፋት እንደሆነ ታጋዩ ፋኖ ያውቃል። ብልጠት ቦታ የለውም።
አሁንም የሚታየው የብልጣ ብልጦች አካሄድ የአማራውን ሕዝብ ትግል በግርግር ለመንጠቅና ሥልጣን ላይ ፊጥ ለማለት የሚሯሯጡ ተረፈ ማርክሲስቶች እጅግ አዋኪ ሆነው ተከስተዋል። ውጭ ሀገር ሆነው፣ ትግሉን ለመደገፍ ብሎ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የለገሰውን ገንዘብ በመቆጣጠር፣ ፋኖን የመከፋፈል አቅም ባገኙ ፕሮፓጋንዲስቶችና የአማራ ትግል ብቸኛ ጠበቃና ስትራቴጂስት ነን ባዮች ታጋዩን ለማዋከብ የሚሞክሩ ብቅ ብለዋል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ ለአገሩ መሲሕ ያገኘ መስሎት በአብይ አህመድ እግር ስር ወድቆ የአገርና የሕዝብ ጠላት እንዲጠናከር ምክንያት እንደሆነው ሁሉ፣ በድንገት ራሳቸውን የፋኖ ተወካዮች ባደረጉ ብልጣብልጦች እግር ስር ወድቆ በላቡ ያገኘውን ሀብት ለማን እንደሚሰጥ ሳያሰላስል፣ ለትግሉ እንቅፋቶችና ከፋፋዮች በማስረከብ አጠቃቀሙን ሳይቆጣጠር ትግሉን ለከፋፋዮች አጋልጧል።
ለምሳሌ፣ ታማኝ በየነ በነበረው ደግነትና የዋህነት የአብይ አህመድን ማንነት ሳይጠይቅ እንደደገፈው ሁሉ፣ ያለመመርመር መንፈሱ በዲያስፖራው ላይ ያደረ ይመስል ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ የፋኖ ተወካይ ነው ሲባል፡ እንዴት? መቼ ገባ? ለምን? ማን ወከለው? ስንት ሠራዊት አላቸው? ብሎ የጠየቀ የለም። በተቃራኒው ይህን ጥያቄ የሚጠይቅ ሁሉ ውጉዝና አርዮስ ሆነ። ብሩን ለሻለቃ ዳዊትና ለኔትወርኩ አስረክቦ፣ ገንዘቡ በትግሉ ላይ እንቅፋት በሚሆን ከፋፋይ መንገድ ተግባር ላይ ሲውል፣ አሁንም ነገሩን ሳይረዳ “አንድ ሁኑ” እያለ ይጠይቃል።
ይህንን ገንዘብ ይዘው ነው ፋኖን በብር ለመግዛት የሚሞክሩት። የሻለቃ ዳዊትና የእሳቸው የፕሮፓጋንዳ ሚኒስቴር የሥልጣን ጉጉት በርካታ የፋኖ ብርጌዶችን እያመሰ ይገኛል። እለት እለት ስልክ እየተደወለ ማን ማንን መምራት እንደሚገባው ትዕዛዝ ይሰጣል። አንታዘዝም የሚሉ ሲገኙ ብር ይነፈጋሉ፤ በተቆጣጠሩት ሚድያ ስማቸው እንዲጠለሽ ይደረጋል።
ከሩቅና በብር በሚዘወር የማይገባ አካሄድ ምክንያት የተነሳው ውዥንብርና ጥርጣሬ፣ እስክንድር ነጋ ከጎጃም እንዲባረር በር ከፍቷል። ትላንት ሕይወታቸውን ለእስክንድር ነጋ የሰጡ ወጣቶች ቢኖሩም፣ ዛሬ ግን ትግሉ የመስዋዕትነት መሆኑ ቀርቶ በዘመነ ካሴና በሀብታሙ አያሌው፣ በእስክንድርና በዘመነ ፉክክር ልክ የሚመዘን አሳፋሪ እንዲሆን እየተደረገ ነው። የዚህ ዓይነት የውስጥ ሽኩቻ ትግሉን የአሳዳጅና ተሳዳጅ እንዳያደርገው ሰግተናል።
አሁን ይህ በሽታ ከጎጃም ወደ ሸዋ እንዲገባ ጥረት እየተደረገ ነውና በዲያስፖራ የምትኖሩ ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስን እባክህ አደብ ግዛ ብላችሁ እንድትመክሩት እንጠይቃለን። በፋኖ ስምም የተሰበሰበውን ገንዘብ ራሳቸውን ለሕዝባቸው የሰጡ ፋኖዎች እኩል ሊካፈሉት የሚገባ ሀብት ነውና ለተመረጠ ኮሚቴ እንዲያስረክብና የፋኖ እዞች እንዳለባቸው ችግር፣ ተጋድሎና የትጥቅ እጥረት እየመዘነ ገንዘቡን የሚሰጥ ኮሚቴ በአስቸኳይ እንድታቋቁሙ እንጠይቃለን።
ይሄንን ስንል፣ በርካታ ምድር ላይ የተሠሩ የፋኖን ትግል ወደ አንድ ማእከላዊ አመራር የመሰብሰብ ሥራዎች እየተጠናቀቁ ነው። በቅርብ ቀን ውስጥ ይህንኑ መላው ፋኖን አንድ የሚያደርግ ፕሮግራም፣ ስትራቴጂና አመራር ይዘንላችሁ እንመጣለን። ፋኖ በሰላማዊ ሰልፍ የጀመረውን ተቃውሞ በሶስት ዙር ወታደራዊ ዘመቻ እራሱን አጠናክሯል። የአራተኛውንና የመጨረሻውን ትግል የምናፋፍምበት ቀን መድረሱን ስንገልጽላችሁ በደስታ ነው። በቅርብ ቀን ትግላችንን በመላው ኢትዮጵያ እናፋፍማለን። የአብይ አህመድ ስርዓት ነዳጁን ጨርሶ ሻማው የሚጠፋበት ቀን ቅርብ ነው።
የኦፒዲኦና የኦነግ ጥምረት የመጨረሻ ተግባሩ ንጹኃንን መጨፍጨፍ ነውና መላው ኢትዮጵያዊ ነቅቶ፣ ዘር ለማጥፋት ከተዘጋጀ ከዚህ ኃይል እራሱን ለመከላከል የሥነ ልቦናና እራስን እንዴት መከላከል እንዳለበት ዝግጅት እንዲያደርግ እንመክራለን። አብይ አህመድ አማራ ክልል ውስጥ የሚኖሩትን ወገኖች ብቻ ሳይሆን በታላላቅ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ አማሮችንና የእርሱን ‘አምላክነት’ የማይቀበሉ የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮችን ለማስጨፍጨፍ የእርስ በርስ ጦርነት የሚመስልና እርሱን ከወንጀል ነፃ የሚያደርግ ጥፋት እያዘጋጀ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ላለመፍቀድ ራሱን ማዘጋጀት አለበት።
ሂትለር በመጨረሻ ሊሸነፍ ሲል ያወጣው አዋጅ ነበር። ይሄም የኔሩ አዋጅ ይባላል። ይህም የጀርመን ሕዝብ በደንብ አልሞተልኝም ብሎ ስላሰበ ከናዚ ፓርቲ በኋላ የጀርመን ሕዝብ መኖር የለበትም ብሎ የጀርመን ኢንዱስትሪዎች፣ የኃይል ማመንጫ፣ ድልድይ፣ ሆስፒታል፣ ሆቴልና ሕንጻዎችን ሠራዊቱ እንዲያወድም አዝዞ ነበር። ይሄንን የታዘዘው አል ርት ስፒርስ የሚባለው የናዚ ሚኒስቴር ትእዛዙን ባለመቀበሉ ነበር ጀርመን የሜርሴዲስ፣ የቢኤም ደብሊው፣ የእነ ባየር ኬሚካል ፋብሪካ ሆና የቀጠለችው።
ስለዚህ የአብይ አህመድ፣ የሽመልስ አብዲሳና የሸኔ መሪዎችም ሂትለር አይሁዳውያንን እንዳደረጉባቸው ሁሉ አማራውን፣ ጉራጌውን፣ ጋሞውን፣ ኦርቶዶክሱን፣ ኦሮሞንም ቢሆን ኢትዮጵያዊነቱን የሚያከብር ከሆነ፥ ነባር ኢትዮጵያዊ እስላሙን፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የሚሉትን ክርስቲያንና ሙስሊም ማጥፋት ነውና ስራቸው ሁሉም ራሱን ከመታረድ ለማዳን የሥነ ልቦና ዝግጅቱን ይጀምር።
ልጄ ታረደ፣ መስጊድ ፈረሰ፣ ቤተ መቅደስ ነደደ፥ ጳጳስ ተንገላታ፥ ካህን በድንጋይ ተወገረ፥ ነፍሰ ጡር ማሕፀኗ ተሰነጠቀ ብሎ ማልቀስ ውጤት አያመጣም። ሕዝብ ኃይል ነውና ኃይላችሁን አሰባስባችሁ ራሳችሁን ከመታረድ አድኑ እንላለን። በሐሰተኛ የሃይማኖትና የባሕል መሪዎች አዳኝነት ከመታለል፥ ወይም በታጣቂዎች ብቻ ተስፋ ከማድረግ ሁሉም ራሱን ያዘጋጅ።
ሕዝብ ብዙ ነውና ሕዝብ ከፍተኛ ኃይል ነው! የነቃ የሚጠይቅ፥ ሌላ ነፃ አውጭና መፍትሔ ሰጭ የማይጠብቅ፥ የሚነጋገር፥ እርስ በርሱ የሚተማመን፥ የሚደራጅ ሕዝብ አሸናፊ ነው። የነቃ ሕዝብ የዘረኝነትና የሐሰት ትርክትና የስሑት ርእዮት ጭፍን መንጋ አይሆንም፤ ጭፍን መንጋዎችንም የመመከት አቅም አለው።
እነ አብይ አህመድ ተስፋ ቆርጠው የመጨረሻውን ዘር የማጥፋቱን ሂደት አሁን እየፈጸሙት ቢሆንም፣ በተለየ ሁኔታ የጅምላ ጭፍጨፋ አዋጅ ሲያውጁ ሠራዊቱም ፖሊሱም ለራሱ ልጅና ሚስት ሲል ወደ ሕዝብ ይቀላቀላል። የጥፋት መልእክተኞችና የዛሬዎቹ መሪዎች ብቻቸውን ይቆማሉ። በመጨረሻም ዘረኝነት አራዊት ያላደረጋቸውና ሰብአዊ ተፈጥሮአቸው ያልተለወጠባቸው እውነተኞች የኢትዮጵያ ልጆች ያሸንፋሉ። ዳግም በሰላም፥ በፍቅር፥ በአንድነትና በእኩልነት የአገር ባለቤት ሆኖ የሚኖር ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያዊነት ከፍታ ይመለሳል።
የአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤት