Fano Unity Council

ፋኖ ለምን አልደራደርም ይላል?

ከፋኖ አንድነት ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

ሰሞኑን የመከላከያ ሰራዊትን እንወክላለን የሚሉ ጄናራሎች፣ የብአዴን ባለስልጣናትና እና በዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በኩል ሆኖ ጃዋር መሀመድ እንዲለጥፈው የተደረገው ጽሁፍ ዓላማው እንድ ነው።

አንደኛ የአምሓራው እራስን ከጥፋት ለማዳን የሚያደርገውን ህዝባዊ መከላከል አቃሎ ለማሳየትና አብይ አህመድ እራሱ “እደራደራለሁ” ሳይል ብልጽግና ለመደራደር እንደሚፈልግ አድርጎ ለማቅረብ ነው። ይህም ሊወድቅ ያለውን ሥርዓት ሰላም ፈላጊ አስመስሎ ለማቅረብና የዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ለማግኘት ነው።

ጃዋር መሀመድ የዛሬ አንድ አመት ገደማ ፋኖ በርካታ ከተሞችን በተቆጣጠረበት ግዜ “የመከላከያ ሰራዊት ሆን ብሎ ነው ከተማ ለቆላቸው፣ ከተማ ከገቡ ቦኋላ ከቦ ያጠፋቸዋል” ብሎ በሙሉ ልብ ተንብዮ ነበር።

ይህ ግምቱ የነ ብርሀኑ ጁላን ትርክት ብዙ በማድመጡ አሁን እንደተሳሳተ የገባው ይመስላል። አምሓራውን ትጥቅ አስፈትቶ መግደል ማሰር ማፈናቀል እንደማይቻል የተረዳ ይመስላል። ከዚህ ቀደም የነበረው ግምት ልክ እንዳልሆነና ፋኖም ዋነኛዎቹ ከተሞችን ያጠቃበት ምክንያቶች፡

አንደኛ ትጥቅና ተተኳሽ እጥረት ለማስወገድ፣

ሁለተኛ ብአዴንን ቀልቡን ለመግፈፍ፣

ሶስተኛ የታሰሩ የፋኖ አመራርና ደጋፊዎች ማስፈታት እና

አራተኛ ፋኖ ሀይል እንደሆነ ለወዳጅም ለጠላትም ለማሳየት ነው እንጂ፡

እነ ባህር ዳርን፣ ደብረ-ብርሀንን፣ እነ ጎንደርን፣ ደሴን፣ ተቆጣጥሮ ለህዝብ ደሞዝ እየከፈለ፣ ዘይትና ጨው እያቀረበ ከተማ ለማስተዳደር እንዳልነበረ እና፡ በጥቃቱም ከተሞችን ለኦህዴድ አየር ድብደባ ለማጋለጥ እልዳልነበረ ገብቶት እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ለሚያስተውል ሰው ግን ምክንያቶቹ እነዚህ እና የመሳሰሉት ናቸው።
የኦህዴድና የኦነግ አክቲቪስቶች አማርኛ ቢናገሩም የአምሓራውን ህዝብ “ቋንቋ” ግን መረዳት እንዳልቻሉ ነው የሚያሳየው።

ፋኖ የማይቆጣጠረው እና የማያስተዳድረው ቦታ አራት ኪሎ ብቻ ነው። እስከዚያው ድረስ ግን፡ ሥርዓቱን በተመቸው ከተማ እየገጠመ ማዳከምና ሥርዓቱ የአምሓራ ህዝብን ትጥቅ አስፈትቶና በተደራጀ ሁኔታ አምሓራን አጥፍቶ የኩሽ መንግስት መመስረት እንደማይችል ለማስገንዘብ ነው።

ይህ ዓላማ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተሳክቷል። አብይ አህመድና ብርሀኑ ጁላ “አምሓራውን በሰራዊት ከብበን ትጥቅ አስፈትተን እንደፈለግነው አሰልፈን እያረድን እንኖራለን” ብለው ነበር። አሁን ግን የአምሓራን ህዝብ ትጥቅ አስፈትቶ ማንበርከክ የሚለው ዕቅድ ወይም ህልም ጠረጴዛው ላይ የለም። ይልቁንም “እባካችሁ ልጆቻችሁን ለምናችሁ አስገቡልን እና አድብተን እናጥፋቸው” ወደሚል የአብይ ልመና ተቀይሯል።

አብይ “ትጥቅ አስፈታለው እንደ ትግራይ ከብቤ አንበረክካለሁ” ብሎ ሰራዊት ሲያዘምት፡ የፋኖ ኃይል በችኮላ የሰለጠነ ወደ 55ሺ ታጣቂ ነበር። ይህም የትግራይ ጦርነት ካለቀ በኋላ እና የአብይ አህመድ በአምሓራው ላይ ያለው ዕቅድ ከወጣ በኋላ በሩጫ ለአንድ ወር እንዲሰለጥን የተደረገ ነበር።

ህወሀትም በአምሓራው ላይ ተረማምጄ አዲስ አበባ እገባለሁ ባለበት ግዜ ሶስት ሺህ የታጠቀ ፋኖ አልነበረም።

አሁን ፋኖ ኩሁለት መቶ ሺህ በላይ የታጠቀና አንድ ዓመት የሽምቅ ውግያ ልምድ ያለው ሰራዊት አለው። እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ እያረሰ የሚበላ፣ ይሁንና ወራሪ ሲመጣ እራሱን ለመከላከል ተጠራርቶ የሚወጣ ሀይልና ድጋፍ ፈጥሯል። ይህንን ማጤን ለወዳጅም ለጠላትም ይበጃል። ስርአቱም አይደፈሬ ነው ብለው በሰራዊቱ ውስጥ መቆየት ይበጃል ያሉም መጨረሻው መቃረቡን ስለተረዱ እየከዱ ከህዝብ ጋር እየተቀላቀሉ ነው።

አምሓራው አሁን ለጠላቶቹ የማይቆረጠም የብረት ቆሎ ሆኖባቸዋል። አሁን አብይም እነጃዋርም የተረዱት እንዳሰቡት አምሓራውን ትጥቅ አስፈትቶ እያፈናቀሉና እያረዱ መኖር እንደማይቻል ነው። ይህ የአብይና የኦሮሙማ ሀይሎች ምኞት በአጭር ተቀጭቷል። አምሓራው ካሁን ወዲያ ጠመንጃውን ተንተርሶ እንጂ ሰቅሎ እንኳን አይተኛም። ይህ የኦፒዲኦ ድንፋታ በሽንፈት እንዲጠናቀቅ አድርጓል።

አሁን ለአብይ፣ ለብርሀኑ ጁላ፣ አበባው ታደሰ ከውስጥ በወርቅነህ ገበየሁና፣ ጃዋር ከናይሮቢ የከፈቱት ዘመቻ “እባካችሁ ጠመንጃችሁን ስጡና አዘናግተን እንረዳችሁ፣ እንጨፈጨፏችሁ፣ እናፈናቅላችሁ፣ እንስደባችሁ” የምትል ማታለያ ነች።

የፋኖ የምዕራፍ ሁለት ትግል ተጀምሯል። አሁን አምሓራን ማዳን ሳይሆን ኢትዮጵያን ከኦህዴድ ጭፍጨፋ ማዳን ነው። ለዚህ ደግሞ የፋኖ ትግል ከወታደራዊ ወደ ፓለቲካዊ ትግል አድጓል። ከኦህዴድ ጋር ሳይሆን ድርድሩ በመላው ኢትዮጵያ ካሉ የዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ጋር ነው።

ፋኖም በስነሥርዓቱና በዓላማው ፅናት ምክንያት ከመላው ኢትዮጵያ ፍቅርና ድጋፍ እያገኘ ነው። ከሥርዓቱ ቀለብተኞች ውጪ መላው ኢትዮጵያዊ ፋኖን እንደ አዲስ የኢትዮጵያውያን አሰባሰቢ አስኳል እየተመለከተው ነው። በርካታ እጃቸውን የሚሰጡ ወታደሮች ከፋኖ ጋር ቆመው የኦህዴድን አምባገነንነት ለመታገል እየሰለጠኑ ነው። በከተማው ያለው በዕብሪተኞች ንብረቱ የሚወድምበት በሰላም ወጥቶ መግባት ያልቻለው ህዝብ ከኦህዴድ አንባገነናዊ ተጽዕኖ ከመላቀቅ መልስ ሰላም እንደማይመጣ ተረድቶ ለፋኖ ሀይሎች የሞራልና የሜዲያ ድጋፍ እያደረገ ነው።

ፋኖ በኢትዮጵያዊነት ስነምግባርና ጨዋነት እራስን ለማዳን እንጂ በሌላው ላይ እራሱን ለመጫን እንዳልተነሳ ሁሉም በመገንዘቡ አብሮ የመስራትና ፋኖን እንደ መላው ኢትዮጵያ መከታነት ለማሳደግ ብዙ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው። ውጤትም ታይቷል።

በሰሜንም በኩል ትግሬን እና አምሓራን በማዋጋት ሁለቱንም በማዳከም ከፓለቲካው ለማስወገድ የተደረገው ጥረትም ከሽፏል።

አሁን ለኦህዴድ መንግስት ከዘረፋና ጭካኔ ውጪ ሀገር ለማስተዳደር እንዳልቻለ ከዛላ አንበሳ አስከ ቶጎ ውጫሌ፣ ከአሶሳ እስከ ደዋሌ ያለው ህዝብ ግንዛቤ ወስዷል።

አሁን፡ በተለያዩ የለውጥ ሀይሎች መሀከል ያለው ውይይት፡ ብዙ ደም ሳይፈስ፣ አብይና ሽመልስ ተጨማሪ፤ ከፈተኛ የዘር ማጥፋት ሳይፈጽሙ፡ እንዴት እናስወግዳቸው? ምን ዓይነትስ የሽግግር ሥርዓት እንፍጠር? የሚል ነው።

በጥላቻና በዘር ማጥፋት የተቀሰቀሰው የኦህዴድ ሰራዊት የአምሓራውን ህዝብ በጅምላ በድሮን በመጨረስ፣ በገቡበት መንደር ሁሉ ማህበራዊ ንቃት አላቸው የሚሏቸውን ሰዎች አሰልፎ በመረሸን፤ ህዝቡ ይህን ግፍ ፈርቶ ከፋኖዎች እንዲሪቅ እና ፋኖዎችን “እባካችሁ ውጡልን” እንዲል ብለው እነ አበባው ታደሰና ሬድዋን ሁሴን እንደ “የቀይ ሽብር” ዓይነት አሰቃቂ ዘመቻ በአምሓራው ህዝብ ላይ እየፈጸሙ ነው። ይሁንና የአምሓራውን ስነ ልቦና አልከፈለውም። ይልቁንም ይሄንን አረመናዊ ሥርዓት ከማስወገድ በቀር ምንም አማራጭ እንደማይኖር ግልጽ አድርጎለታል።

ምንም የሌለው የአምሓራ ገበሬ ከ200 ሺ በላይ የሚሆን ሰራዊት፡ እንጀራ እየጋገገረ፣ ወጥ እየሰራ የፋኖን ጦር እያበላ እያጠጣ ነው።

የአምሓራው ህዝብ ትግል አሁን ከመከላከል ወጥቶ ወደ አጥቂነት የሚሸጋገርበት ቀናት ቅርብ እንደሆነ የመከላከያ ሰራዊቱም ከዚህ በላይ የመሞት ፈቃደኝነት እንደሌለው በሚማረከው ወታደር ቁጥር እየተገለጸ ነው።

ስለዚህ የአብይ አህመድን ሥርዓት ለማዳን ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁና ጃዋር መሀመድ በናይሮቢ የሀብታሞች ሰፈር ቪላ ገዝተው ቡና እየተጠራሩ የጀመሩት ዘመቻ ትግሉን ለማዘናጋት እና ኢትዮያውያንን ለማሳሳት ነው።

“አብይ አህመድ ሊገድለኝ ይፈልጋል” ብሎ የሸሸ አማጺ ከሥርዓቱ ደጋፊ ጋር በአንድ ግቢ ውስጥ አይኖርም።

መጀመሪያ፡ የፋኖን አንድ ያለመሆን እንደምክንያት እያቀረቡ ፋኖ ዓላማና ግብ የሌለው ለማስመሰል ተጥሮ አልተሳካም። አሁን ደግሞ መንግስት ለመደራደር እንደሚፈልግ ይሁንና ፋኖ እምቢ እንዳለ ለማስመሰል ጥረት እየተደረገ ነው። ምክንያቱም ምዕራባውያን “አብይ ምን አማራጭ አለው ከመዋጋት በቀር?” ብለው ከዓለም ባንክ ዶላር እንዲለቀቅለት ነው።

የፋኖ መሪዎችና ወኪሎች በተደጋጋሚ ከበርካታ የአሜሪካና የአውሮፓውያን አምባሳደሮችና ተጽእኖ ፈጣሪዎች ጋር ተገናኝተዋል፣ በስልክ መስክ ላይ ካሉ ወታደራዊ አመራሮች ጋር ብዙ ግዜ ተወያይተዋል። የምዕራቡ ዓለም የአብይን፣ የሽመልስን እና የአዳነች አቤቤን የዘር አጥፊ “ኢንተርሀምዌ” ዓይነት ሰራዊትና ዝግጅት በቅርብ ይከታተላሉና እያሳሰባቸው ያለው የዚህ የኦህዴድና የኦነግ የዘር ማጥፋት ዝግጅት እንጂ የአብይ ስልጣን ላይ መቆየት አይደለም።

አሜሪካውያኑ እና አውሮፓውያኑ የፋኖን ዓላማና ግብ ጠንቅቀው ያውቃሉ። በአምሓራው ህዝብ ላይ የታቀደው የዘር ማጽዳት ዘመቻም እንደሚያሳስባቸው በዲፕሎማሲ ቋንቋ ገልጠዋል።

ጃዋር “ፋኖ በፕሪቶሪያ ስምምነት አኩርፎ ነው ከመንግስት ጋር የተጣላው” የሚለው ሌላው የማቃለል ሙከራ ነው።

ግፈኞቹ እውነቱ ጠፍቷቸው ባይሆንም፡ እውነቱን ለማስረገጥ ያህል፡ ፋኖ ጠመንጃ ያነሳው፡ በወለጋ፣ በአርሲና በመላው ኦሮምያ የሚጨፈጨፈውን የንጹሀን ህይወት ለመታደግ ነው። የትግራይ ጦርነት ሲጀመር አንድ ሺ የፋኖ ታጣቂ አልነበረም። በየ ዕዙ ያለው ከ200 ሺህ በላይ ትጥቅ ያለው ፋኖ የተደራጀው መንግስት አምሓራውን ትጥቅ አስፈታለሁ ብሎ ከዘመተ በኋላ ነው።

ፋኖ የተደራጀው ልጆቻቸውን፣ ሚስታቸውን፣ እናታቸው እና ንብረታቸውን ወደ ቀያቸው ከመጣው ወራሪ ለመከላከል ነው። እነ እሸቴ ይታገሱና እነ ሞገስ እሸቴ የተሰዉት በቤታቸው በማሳቸው እንጂ መቀሌ አይደለም የሞቱት። ስለዚህ የጃዋር የማቃለል እርምጃ በእውነት ላይ የተመሰረተ አይደለም።

አሁን በትንሹ 200 ሺ ክላሽ፣ ዲሽቃ፣ ቦንብ የታጠቀ፣ በወታደራዊ አደረጃጀት መዋቅር የፈረጠመ፣ የጸና ወታደራዊ አቅዋም እና መለያ ያለው ኃይል አለ። ከዚህ ጀርባ ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠር ቀን አርሶ ማታ ደግሞ ታጥቆ ቀዬውን የሚጠብቅ ህዝባዊ ሰራዊት ነው የገነባው። ይህ ኃይል በሰፈሩ፣ በሚያውቀው ጋራና ሸንተረሩ፣ በራሱ ወንዝ እና ጫካ ያለ ስለሆነ አምስት ሚሊዮን ሰራዊት አብይ አህመድ ቢያሰማራም የአምሓራውን ህዝብ ድል ማድረግ እንደማይችል ግልጽ ሆኗል።

ስለዚህ የፋኖ ትግል በሻሸመኔ፣ በአርሲ ኔጌሌ በወለጋ በአምሓራ ላይ የተፈጸመው ዓይነት ጭፍጨፋ፣ በመረሀቤቴ፣ በአጣዬ እያለ ወደላይ እየገፋ መምጣቱን ስለተረዳ ነው። ንጹሀን እየታረዱ በዶዘር ሲቀበሩ፣ ህጻናት ልጆች “ወላሂ ሁለተኛ አምሓራ አልሆንም!” ሲሉ በማየቱ ነው። የኦህዴድ ሥርዓት ግብ የአምሓራውን ዘር ማጥፋት መሆኑን ስለተረዳ ነው።

ፋኖ ህወሓት ለ27 ዓመታት በአምሓራው ላይ ሁሉን አሰባስቦ ያደረገውን በደል ባይረሳም ከሁሉ በላይ ግን እራሱ ባሳደጋቸው ከአብራኩ በወጡ ጸረ-አምሓራ ውሾች ተግጦ አጥንቱ ነው የቀረው።

ፋኖ በትግራይ ህዝብና በህወሓት መሀከል ያለውን ልዩነት ያውቃል። ለዚህም ነው ችግሮቹንና ልዩነቶችንንም በሰላማዊ ንግግርና በስምምነት ከትግራይ ጋር እንዲፈታ ሶስት ወኪሎች መርጦ

፩ኛ: ዶክተር ወንድወሰን አሰፋን

፪ኛ፣ ጄኔራል ተፈራ ማሞን፣

፫ኛ፣ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔን

ወክሎ ከህወሓት ጋር ለመደራደር ወደ ፕሪቶርያ ለመሄድ መንግስትንና አደራዳሪዎችንም ጠይቆ የነበረው። መንግስትም አደራዳሪዎቹም ጥያቄውን ንቀው የአምሓራው እጣ ፈንታ በኦህዴድ ጀነራሎች እንዲወከል ተደርጓል። ይህም የሆነበት “አምሓራውን፣ ትግሬውንና ኤርትራውን እርስ በእርስ አዋግተን ከአዳከምን ቀይ ባህር ላይ ኢሬቻን እናከብራለን” ብለው ያሰቡትን እቅድ ስለሚያከሽፍ ነበር።

የፋኖ አንድነት ምክር ቤት በቅድመ ድርድር ላይ ያለው አቋም።

በሁሉም ሀገራት ቅድመ ድርድር የሚባል እሳቤ አለ። አብይ አህመድ በድርድር ችግሩ እንዲፈታ ከፈለገ በመጀመሪያ ከአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ውጪ ያዘመተውን ጦር ወደ ካንፑ ይመልሳል እንጂ አዲስ ጦር አያዘምትም። በነዚህ ምክንያቶች ነው ፋኖ አልደራደርም ያለው።

፩ኛ፣ ለዚህ የይስሙላ የ “እንደራደር” ጥሪ የፋኖ አቋም የሚመሰረተው፡ የብልጽግና ፓርቲ ህጋዊ ተቋም አለመሆኑ እና አቢይ እና ሌሎቹም ተዋናዮች ሁሉ ለህግ የማይገዙ መሆኑን፡ ይህም በተደጋጋሚ በግልጽ የታየ መሆኑን በማጤን ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለይስሙላም ቢሆን ፓርላማ ተሰይሞለት ነበር። ይህ ፓርላማ ለቪዲዮ ቀረጻና ለማጨብጨብ ብቻ የሚጠራ ሆኖ ፓርላማው ተበትኗል። ስራ አስፈጻሚውን ውሳኔ ተወያይቶ የሚያጸድቅ ከዛም የሚቆጣጠር ሥርዓት በሌለበት ምንም አይነት ስምምነት አይጸናም።

፪ኛ፣ የኢትዮጵያ የሃገር መከላከያ ሰራዊት የተቋቋመበት ዓላማ እና ህግ የኢትዮጵያን ህዝብንና ዳር ድንበር ማስከበር ቢሆንም በኦህዴድ ጄኔራሎች ተጠልፎ የአንድ ሰው አሽከር ሆኗል። ገለልተኛ ሰራዊት በሌለበት ሀገር የድርድር ስምምነትን ማጽናት አይቻልም። በአለፋት ስድስት አመታት ለኦህዴድ አድሮ ኢትዮጵያውያንን እንደ ጠላት መድቦ በኦሮሞ፣ በአምሓራ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ ዘመቻና ጭፍጨፋ ሲፈጽም ነው የታየው።

ለህዝብም ለህገ መንግስትም አንገዛም ያሉ ጀኔራሎች በአንድ ሺህ ካሬ ሜትር የአዲስ አበባ መሬትና በ7 ሚሊዮን ብር የቤት ማሰሪያ ድርጎ ሰራዊቱን ወደ ቅጥረኛ/ሜርሲነሪ/ ተቋም ቀይረውታል።

ፋኖ በሰራዊቱ ውስጥ፡ በተለይም በበታች መኮንኖች እና በተራው ወታደር ውስጥ ያለውን የቁጭት መንፈስ ይረዳል። በቅርብ ግዜ የበታች መኮንኖች ተደራጅተው በከተማ ቦታ እና በ7 ሚሊዮን ብር የተሸጡትን ጄኔራሎች እያሰሩ እርምጃ መውሰድ ቢጀምሩ ምናልባት ለውጥ ሊመጣ ይችል ይሆናል። እስከዚያው ድረስ ግን በፋኖና በኦህዴድ መሀከል ስምምነት ቢደረስ ሰራዊቱ በገለልተኝነት ስምምነቱን ለማስከበር ይሰራል ተብሎ አይታመንም። በገለለልተኛ ሰራዊት በሌለበት እና በማይጠበቅ ስምምነት ትርጉም የለውም።

ሰራዊቱ “ለምንድነው በህዝብ ላይ የምዘምተው? እኔ የግለሰቦች አሽከር አይደለሁም፣ የምሞተውስ ለማን ነው?” ብሎ መጠየቅ እስከሚጀምር ድረስ ስምምነት የሚጠብቅ እና የሚያጸና ሀገርዊ ሰራዊት የለም።

፫ኛ፣ እጅግ በአጽንዖት ሊተኮርባቸው እና ሊጤኑ የሚገባቸው ጉዳዮች፡ የአምሓራ ህዝብ ያመጸባቸው ጥያቄዎች ግልጽ መሆናቸው እና እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ምንም ድርድር አለማስፈለጉ ነው። ይልቁንም የሃገሪቱን ህግግጋት እና ሥርዓታት ማክበር ብቻ ዋናውን ችግር ይቀርፋል።

እነዚህንም ጥያቄዎች እንደሚከተለው በጥቅሉ ማስቀመጥ ይቻላል።

1ኛ፣ በአምሓራው ህዝብ ላይ በመላው ኦሮሚያ በመካሄድ ላይ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ይቁም ነው። እነ አበባውና አገኘሁ ተሻገር እየዞሩ የሚሉት ደግሞ እናንተ እጃችሁን አጣጥፋችሁ ተቀመጡ በወለጋ በአርሲ በመላው ኢትዮጵያ አምሓራ መታረዱ ይቀጥላል። እኛ ንብረት መዝረፍ፣ ዘር ምጥፋቱ እንጂ ማስቆም ሀላፊነታችን አይደለም ነው የሚሉት። ኦፒዲዮ ወንብፕዴ ባይሆንና መንግስት ቢሆን ኖሮ የስቸፈታችሁበትን ጉዳይ አስወግደናል፣ ከዛሬ ወዲህ አምሓራ የማይታረድበት ስርአት መስርተናል ይሉ ነበር። የሰውን በህይወት የመኖር መብት ያልቆመ ጄኔሬል አበባው በምን መንገድ ነው ጠመንጃችሁን ስጡ የሚለው? የሰው ልጅ በህይወት መኖር ማረጋገጥ የመንግስት ግዴታ ወይስ በድርድር የሚገኝ መብት ነው? ይህ ምንም ድርድር አያስፈልገውም በህይወት መኖር መብት ነው።

2ኛ፣ የአምሓራው ህዝብ በሀገሩ ላይ እንደ እኩል ዜጋ ይታይ፣ የመንቀሳቀስ፣ የመስራት፣ ሀሳብን የመግለጽ፣ የመምረጥ፣ የመመረጥ፣ በህግ የመዳኘት፣ ንብረቱ አለመወረስ፣ አለመፈናቀል፣ ከህግ ውጪ መታሰርና መንገላታት ይቁም ብሎ መጠየቅ በድርድር የሚረጋገጥ ሳይሆን ህጋዊ መብት ነው። እነዚህ በህገመንግስቱ እና በአለማቀፋዊ ህግግጋት የተደነገጉ የሰው ልጆች መብቶች ናቸው። እነ አበባው በአንድ ሺ ካሬ ማትር ቦታና እና 7 ሚሊዮን ድጎማ ቤት ሲሰሩ በመላው ሀገሪቱ ንብረቱ እየወደመበት ያለውን አምሓራ ማስቆም የነ አበባውን የነ ተመስገን ጥሩነህ ተግባርና ሀላፊነት አይደለም ብለው ነው የሚያስቡት። ይሄንን ፋኖ መንግስትን ጠይቆ፣ ተደራድሮ፡ ሳይሆን የሚያከብረው የመንግስትነት ግዴታዎች ስለሆኑ ብቻ ነው።

3ኛ የአምሓራ ህዝብ በሽመልስ አብዲሳ በሚመራው ሰራዊት፣ በጃል መሮ የሚመራው የኦሮሞ ነጻ አውጪ፣ በብርሀኑ ጁላ የሚመራው በኢትዬጵያ ስም የሚጠራው የኦህዴድ አመራር፣ በአዳነች አቤቤ የሚመራው የአንድ ጎሳ ጠባቂ ሀይል፣ በአብይ አህመድ የሚመራው ሪፓብሊካን ጋርድ ሁሉ አምሓራውን ትጥቅ አስፈትተው “ዘሩን እናጠፋዋለን” በሚሉበት ሀገር፡ አምሓራው “ትጥቄን ፈትቼ ወለጋ ውስጥ እየታረዱ እንዳሉት ወገኖቼ አልታረድም” ነው ያለው። ትጥቅ ደግሞ የአምሓራው ህዝብ ባህልና እሴት ነው። ትጥቅ በመታጠቁ ነው በሶስት ሺህ ዘመን ኢትዮጵያን በነፍስ ወከፍ መሳሪያ፣ በራሱ ትጥቅና ስንቅ ሀገሩን የጠበቀው። ይሄንን መብቴን አክብሩልኝ ነው ያለው። ይሄንን መብት ለማክበር ምንም ድርድር አያስፈልግም።

4ኛ፣ “ብአዴን” የሚባል ለሆዱ ያደረ ቅጥረኛ እራሱ ባመነው ለ27 ዓመት አምሓራውን አሰቃይቶታል። ሁለተኛ እድል ቢሰጠውም አምሓራን እያረደ መኪናና ቪላ ነው እየተቀበለ ያለው። ብአዴን አምሓራውን መወከልና ለአምሓራው መብት መቆም አይፈልግም፣ አይችልም። በወለጋ፣ በአርሲ፣ በቤንሻጎል፣ እና በመላው ኦሮምያ ንጹሀን አምሓሮች ሲታረዱ የሚጣልለት ፍርፋሪ እንዳይቀርበት ድምጽ አሰምቶ አያውቅም። ስለዚህ የአምሓራ ህዝብ “በቃኝ!” ማለቱ መብቱ ነው። “እኔው ራሴ በመረጥኳቸው ልጆቼ ልተዳደር!” ማለቱን ለማክበር ምን ድርድር ያስፈልገዋል? የትግራይ ህዝብ “ይወክለኛል” ብሎ ያመነውን የመሪዎች ድርጅት ደግፎ በማመጹ ምክንያት ህወሓት እንደቀጠለው ነው። አምሓራውም በሚፈልገው መሪዎች ይወከል፣ ይተዳደር ማለት ምንም ድርድር አያስፈልገውም። መንግስት የ “አማራ ክልል”ን ፕሬዚዳንት እንደ የሽንት ጨርቅ እየተጠቀመ እንደሚጥል እና ምን ያህል ጊዜ እንደቀያየራቸው ታይቷል። ይህን ግፍ ማስቀረት የህዝብን መብት በማክበር እንጂ በድርድር አይፈታም።

5ኛ፣ የአምሓራ ህዝብ ባንክ አልዘረፈ፣ ተቋሟት አላቃጠለ፣ ንጹሀንን አፍኖ ብር አልተቀበለ፣ ሰው አልገደለ። በዚህ ሁሉ ጦርነት ውስጥ፡ ህግ አክብሮ በሰላም የሚኖር ልዩ ህዝብ ነው። አምሓራው በሰላም ያለ መንግስት ጥበቃ በሚኖርበት ሀገር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ሰራዊት ማዝመት፡ ኦህዴድ አምሓራን ለማጥፋት ካለው ዕቅድ ውጪ ህጋዊነት የለውም። ስለዚህ በአምሓራው ላይ የዘመተው ሰራዊት ከክልሉ ይውጣ፣ ምድቡ በክልሉ ውስጥ የሆነው ክፍለጦር ወደ ካንፑ ይመለስ ነው።

6ኛ፣ የክልሉ የአድማ በታኝ ተብሎ 11 ሺህ ብር ደሞዝ እየተከፈለው አምሓራን የሚገድለው የቅጥረኛ ሀይል ይበተንና ህዝቡ በሚያቋቁመው ሀይል ይተካና የአካባቢውን ሰላም ያስጠብቅ ነው። ለመከላከያ ወታደር 3000 ሺህ ብር እየከፈለ ከአምሓራው በቀረጥ የተሰበሰበውን ብር ለቅጥረኛ ሀይል 11ሺ ብር የወር ደመዎዝ መክፈል ወንጀል ነው። ይሄንን ለማቆም ምን ድርድር ያስፈልጋል?

7ኛ፣ አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጣበት ጊዜ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ቢያንስ ቢያንስ 98% የሚሆነው ህዝብ፡ ድጋፍ ሰጥቶት ነበር። ይሁንና ባለበት የአእምሮ ቀውስ ሁሉን ጠላት አድርጎ መላው ኢትዮጵያ ጠመንጃ እንዲያነሳ ተገዷል። በትግራይ፣ በአምሓራ፣ በአፋር፣ በሱማሌ፣ በቤንሻንጉል፣ በኦሮምያ የትጥቅ ትግል ተቀጣጥሏል። በደቡብና በአዲስ አበባም ሰዉ አይታጠቅ እንጂ ልቡ ሸፍቷል። ኢኮኖሚውም ላይ ያለው ውድቀት የገና ዛፍ ላይ መብራት በማብራትና ጨሌ በማንጠልጠል ሊሸፋፍን አልተቻለም። ፓርላማውን ከሥራ ውጪ አድርጎ፣ ሰራዊቱን የግል አሽከር አድርጎ፣ ፈጠርኩም የሚለው የብልጽግና ፓርቲ ገባዔ ሳያደርግ “እኔ መሪው ነኝ” ብሎ እራሱን የመረጠው ንጉስ ነኝ ባዩ አብይ አህመድ ብቁ አይደለምና “ስልጣኑን እንደ ኃይለማርያም ደሳለኝ ይልቀቅ” ነው። በኢትዮጵያ ህዝብ ስም የሚሰበሰበውን ምጽዋት ለግልና ለልጆቻቸው ምቾት በቢሊዮን ዶላር አያባከኑ እና የኢትዮጵያን ህዝብ ንብረት ለቅንጦት ቤተ መንግስት ኝባታ አይዋል ነው። ይህንን ማስቆም የፓርላማ እንጂ በፋኖ ድርድር ጥያቄ አይደለም። ስለዚህ አብይ አህመድ በፈጠረው የሃገር ክህደትና የህዝብ ንብረት ብክነት ስልጣኑን ይልቀቅ ነው። ይህን ጥያቄ እንስቶ ለደራደሩ የሚገባቸው “ፓርላማ” ውስጥ የተሰየሙት “የህዝብ ተወካዮች ነን” የሚሉት ናቸው። ለዚህ ከፋን ጋር ድርድር አያስፈልግም።

8ኛ፣ ለአምሓራው ህዝብ ድምጻቸውን ያሰሙትን ያለአግባብ በየቦታው የታሰሩትን ይልቀቅ ነው። ይህ የፍርድ ቤትና የፓርላማው ሀላፊነት እንጂ ነጻ ዜጎችን በድርድር ማስፈታት የፋኖ ስራ መሆን የለበትም።

ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች ለመተግበር ምንም ድርድር አያስፈልግም። በየ አደባባዩ፣ በየ ህዝባዊ አዳራሹ፣ በየ ሶሻል ሚዲያው በየቀኑ የሚቀርቡ ናቸው። ብዙ የማንስማማበት አንቀጾችም ቢኖሩትም፣ በሃገሪቱ ህገ መንግስት ላይ እና በዓለማቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ላይ የተደነገጉ ስለሆነ “የዘር ማጥፋት አቁምልን ብሎ” ከመንግስት ጋር የተደራደረ ሀይል የለም። ፋኖም በህይወት የመኖር መብት ይሰጠኝ ብሎ በድርድር አይጠይቅም። ምክንያቱም ሁላችንም በህይወት የመኖር መብት አለንና!