የወለጋ ክፍለ-ሀገር ፋኖ ዕዝ (ቢዛሞ) ምስረታን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

የወለጋ ክፍለ-ሀገር ፋኖ ዕዝ (ቢዛሞ) ምስረታን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

እኛ በቀድሞ ዳሞትና ቢዛሞ ግዛት በዛሬው ወለጋ ክፍለ ሃገር የምንኖር የአማራ ህዝቦች  በአጠቃላይ ከባለፉት 450 ዓመታት ጀምሮ በእመቃ፣ በስልቀጣ ከፍ ሲልም የጅምላ ጭፍጨፋ እየተፈፀመብን በርካታ የመከራ ዘመናትን አሳልፈናል።ቅድመ አያቶቻችን ባቆዩት ሀገር አገዛዙ በንቃት በፌደራሉም ሆነ በክልል ምክር ቤቶችም ሆነ ስራ  አስፈፃሚነት ቦታ እንዳይኖረን በማድረግ ሁለተኛ ዜጋ አድርጎን ቆይቷል።

በተለይም ደግሞ ባለፉት 6 ዓመታት አብይ አህመድ በቀጥታ በሚመራው የጥፋት ፕሮጀክት አማካኝነት ከታሪክ፣ ከባህል፣ ከቋንቋ፣ ከማህበራዊ ግንኙነት ተፅዕኖ ባሻገር በህይወት የመኖር መብታችንን ተነፍገን ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሞብናል።
በዚህ አካባቢ የሚገኘው የአማራ ህዝብ ህልውናውን ለማስቀጠል የሚያደርገው ተጋድሎ በበቂ ሁኔታ በመደራጀት፣ በመሰልጠን፣በመረጃ ልውውጥና በመታጠቅ ረገድ በርካታ ጉድለቶች ያሉበት ከመሆኑም ባሻገር ተጋድሏችን በአንድ የእዝ ሰንሰለት ውስጥ ባለመሆኑ የሚጠበቀውን ወሳኝ ውጤት ማምጣት አልቻለም::

በዚህ መሰረት አንድ በመጥፋት ላይ ያለ ማህበረሰብ  ተደራጅቶ እራስን የመከላከል ተፈጥሯዉ መብታችንን በመጠቀም በተደራጀ ሁኔታ እራሳችንን ለመከላክል የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

1)  እኛ በቀድሞ ዳሞትና ቢዛሞ በአሁኑ  የወለጋ ክፍለ ሀገር ፋኖ ዕዝ( ቢዛሞ) በተጠናከረ ሁኔታ ለመደራጀትና እራሳችንን ለመከላከል ቆርጠን የተነሳን መሆኑ በድጋሜ እናረጋግጣለን።

2)  ባለንበት ቀጣና በሁሉም መስክ ተጠናክረን እንድንወጣ ሁለተናዊ ድጋፍ ላደረጉልን የአማራ ፋኖ በጎጃም እጅግ ታላቅ ምስጋናችንን እያቀረብን ለወደፊትም የላቀ ትብብር እና ድጋፍ እንደምናገኝ ወንድማዊ መተማመናችንን እንገልፃለን።

3)  ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ጋር በደስታም ፤በመከራም ክፉ ደጉን አብረን ያሳለፍን በጋብቻም፣ በማህበራዊ ኑሮ መስተጋብርም አብረን የኖርን በመሆኑ ፤ በሥልጣን ላይ ባሉ ጥቂት የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በአረመኔነት በላያችን ላይ የጫኑትን ፀረ አማራ እና ፀረ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ቡድኖችን በጠላትነት የፈረጅነውን ያህል እንደ ህዝብ የአማራና የኦሮሞ ህዝብ በጠላትነት ይተያያል ብለን አናምንም። ስለሆነም ትግላችን የህልውና ትግል ነውና ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ትግላችንን በአወንታ ተመልክተህ ከጎናችን እንድትቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

4)  መላው አማራ ና የኢትዮጵያ ህዝብ አያት ቅደመ አያቶቻችን ባቀኑት፣ተወልደን አድገን ወግና ማዕረግ ባየንበት አገራችን እየተገደልንና ከፊል ወገናችን በተለያዩ የተፈናቃይ ስደተኛ ጣቢያዎች ታጉሮ በርሃብና በበሽታ በሚረግፍበት በዚህ ሰዐት ታግሎ ከማሸነፍ ውጭ አማራጭ የለንም እና በተቻላችሁ ሁሉ ይህንን የህልዉና ትግል  በሞራልም በሃሳብም ድጋፍ ታደርጉልን ዘንድ ጥሪ እናስተላልፋለን።

5/ በውጭ የምትገኙ ወገኖቻችን እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ትግላችን ህልውናን የማስጠበቅ መሆኑን ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ እንድታሳቁ፣  በሎጅስቲክና በሃሳብ  ድጋፍ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

6/  በአማራ ክልል በተለያዩ ቀጥናዎች የምትገኙ የፋኖ አደረጃጀቶች ድጋፍ እንድታደርጉልን ወንድማዊ ጥሪ እናደርጋለን።

7/  ከወለጋ ተፈናቅላችሁ በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ለምትሰቃዩና በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ተበታትናችሁ የምትገኙ እህት ወንድሞቻችን የገጠመን ጠላት ብንሸሸው ብንሸሸው ያለንበት ቦታ ድረስ መቶ የሚያጠፋን ስለመሆኑ በወሎ እና በጃዊ ተፈናቃዮች ላይ የደረሰው በቂ ማሳያ ነው። በመሆኑም ወጣቶች ወደ ቀያችሁ እንድተመለሱና የህልውና ትግሉን እንድትቀላቀሉ ጥሪ እናስተላልፋለን።

8/  በወለጋ በተለያዩ አደረጃጀቶች ታቅፋችሁ የህልውና ትግል እያደረጋችሁ ያላችሁ ወንድሞቻችን ትግላችን በአሸናፊነት የሚቋጨው ኃይላችንን በጋራ አደራጅተን ስንመራ መሆኑን ተገንዝባችሁ ድርጅታችንን እንድትቀላቀሉ ጥሪ እናደርጋለን።

9/  ከአማራ ህዝብ አብራክ ወታችሁ ከፀረ አማራ ኃይሎች ጋር ሁናችሁ በህዝባችን ላይ የዘር ማጥፋት ድርጊት ከሚፈፅሙት ጋር ቀጥተኛ  ተሳታፊ የሆናችሁ አካላት ከድርጊታችሁ እንድታቀቡ ስንል ጥሪ  እናስተላልፋለን።

ድል የህልውና አደጋ ለተጋረጠበት የአማራ ህዝብ !!! ድል ለአማራ ፋኖ!

የወለጋ ክፍለ ሀገር ፋኖ ዕዝ(ቢዛሞ)
ታህሳስ 8/2017 ዓ.ም ወለጋ /ቢዛሞ/ ኢትዮጵያ!