ከአማራ ፋኖ በሸዋ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ!
የአማራ ፋኖ በሸዋ 2ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ለአስራ አራት ቀናት ያህል አካሂዷል፡፡ ጉባኤዉ በርካታ ነገሮች የተዳሰሱበት፣ በትግል ሂደት ወቅት የነበሩ ጥንካሬና ድክመቶች የተፈተሹበት፤ የተለያዩ ማሻሻያዎችና እርምቶች የተወሰዱበት በመሆኑ ለሞት ሽረቱ ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት የወሰደ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ይህንን ጉባኤ ለየት የሚያደርገው የአብይ አገዛዝ ከመደናበር ወደ ለየለት ሙሉ ሽንፈት በተንደረደረበት ብሎም አስተዳደሩ ተፈረካክሶ በምትኩ የፋኖ መዋቅር እስከታችኛው እርከን የተዘረጋበት። ከስጋ-ደም ህልውና ወደ አጽመ-ሬሳ አፈርነት የአገዛዙ የህልውና የተሸጋገረበት ወቅት መደረጉ ነው፡፡
በሌላ በኩል ይህ ጉባኤ በውስጣችን ሰርጎ ገብቶ የነበረውን እፉኝት ከነ መርዙ፣ እባጭ ከነ ሰንኮፉ ነቅለን ባስወገድንበት ብሎም ወደ ነበረን የትግል ስልት በአንድነት መጓዝ በጀመርንበት ማግስት መሆኑ የጉባኤዉን ድምቀት ያጎላዋል፡ፋኖ ብሶት የወለደው ምሬት ያበቀለው መገፋት የገፋው የግፍ በቃኝ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ፋኖ ማንም ነው! የትም ነው! መቼም ነው! ፋኖ የትዳር-ጎጆ ባልደረባ… የሰርግ-የለቅሶ ታዳሚ የመንደር-ቀዬ ባለድርሻ ግን ደግሞ ሁሉም እንዳልሆነ የሆነበት የህዝብ የአርነት ትግል ነው፡፡
ፋኖ የአራሽ ገበሬ፤ የቀዳሽ ካህን፣ የሱቅ ገበያ ነጋዴ፣ የምሁር ተማሪ አጀብ፣ ብሎም የትንሽ ትልቅ የሰቆቃ ድምጽ ነው፡፡ ፋኖ ጾታ፣ እድሜ፣ ስራና ቦታ ያልገደበው ዋይታና ኡኡታ ያለበት፣ ምልጃና ጸሎት ምሱ የሆነ፣ መጣልና መውደቅን ለነጻነት ግብር የሚከፍል ቁርጠኝነት ነው፡፡
የዘንድሮዉ ጉባኤም ይህንን ሁሉ መታደል ታሳቢ ባደረገ መንገድ የተካሄደና በመጨረሻም በሚከተሉት ጭብጦች ላይ ውሳኔ ያሳለፈና አቅጣጫ ያስቀመጠ ጉባኤ ነበር፡፡
1ኛ. ባለፉት አስር ወራት የፋኖ እንቅስቃሴ ምን ይመስል እንደነበረ ተገምግሟል፡፡ በትግል ሂደታችን በርካታ ድሎችን በተለያዩ ቦታዎች አስመዝግበናል፡፡ የአብይ አገዛዝ ሰራዊትን በመደምሰስ፣ ሎጀስቲክ በመማረክ ብሎም አስተዳደራዊ እንቅስቃሴውን በማኮላሸት ረገድ አንቱ የሚያስብል ስራዎችን ሰርተናል፡፡ የሰራዊታችንም ቁመና በጥራትም ሆነ በብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንደሆነ ገምግመናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሊስተካከሉና ሊጎለብቱ የሚገቡ ነገሮችንም በስፋት በመወያየት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል በተጨማሪም ድርጅቱ ከተመሠረተ ጀምሮ የነበረ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ኦዲት ቀርቦ የተገመገመና በውስንነቶቹ ላይ የማስተካከያ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡
2ኛ. የትግላችን አንዱ ማነቆና ፈተና የነበረው እንደ አማራ ያለን አንድነትና ህብረት ነው፡፡ ይህም ቢያንስ በሁለት መንገድ ልንመለከተው እንችላለን፡፡ አንደኛው በሴረኛው አገዛዝ መርዝ ተጠምቀዉ በሰረጉ አለያም የራሳቸውን የመርዝ ተፈጥሮ ይዘውብን በተጠጉን ትግል ጠላፊዎች እና የአማራን የህልውና ትግል ለፖለቲካ ትርፋ በሚፈልጉ ምክንያት የተፈጠረ ችግር ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ በውስጣችን ባሉ የራሳችን አባላት የዋህነት አለያም በአላቸው አነስተኛ ግንዛዜ ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነው፡፡
ምንም ይሁን ምንም ልዩነት ለማንም የማይበጅና ትግላችንን የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን ወደ ኃላ የሚጎትት በመሆኑ በአጽንኦት የምንቃወመዉና በጽናት የምንታገለዉ የተወገዘ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን ተግባር በአንክሮ የሚከታተልና ሂደቱን የሚያሳልጥ አንድ ግብረ ሀይል ተቋቁሟል፡፡ በዚሁ መሰረት እንደ ሸዋም ሆነ እንደ አማራ የጠነከረ አንድነትና ዉህደት ያለው የአማራ ፋኖ ትግሉን ለድል እንደሚያበቃዉ ይጠበቃል፡፡
3ኛ. ይህ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ለአሰራር እንዲያመች የመዋቅር ማሻሻያዎችን በመገምገም አጽድቋል፡፡ በዚሁ መሰረት የስያሜና ሎጎ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ “የአማራ ፋኖ በሸዋ ዕዝ” የሚለው ተቀይሮ “የአማራ ፋኖ በሸዋ” በሚል ተተክቷል፡፡ በሌላ በኩልም የድርጅት ጉዳይ፣የድርጅት ጽ/ቤት፣ የአስተዳደር ጉዳዮች ብሎም የፍትህ መምሪያ በመዋቅር እንዲካተቱ ተደርገዋል፡፡
4ኛ. በድርጅታችን ጉባኤ የትኩረት አቅጣጫ ከነበሩት መካከል የተለያዩ መመሪያዎችንና የአሰራር ስርአቶችን ተወያዮቶ ማጽደቅ አንዱ ነበር፡፡ በዚሁ መሰረት የአስተዳደር ጉዳዮች መመሪያ፣ የፋይናንስ አስተዳደር መመሪያና ሌሎች ጉዳዮች ቀርበዉ እንዲጸድቁ ተደርገዋል፡፡
5ኛ. ከዚህ በተጨማሪ በጉባኤዉ የአመራር ሽግሽግና መተካካት ተካሂዷል፡፡ ከነበረን ግምገማ ውጤት በመነሳት ቀጣይ የሚጠበቅብንን ተግባርና ትግሉን ወደ መቋጫ ለማድረስ ከሚደረግ መራራ ትንቅንቅ አንጻር የሰው ሀይል ምደባ አድርገናል፡፡ ዋናዉ መስፈርትም የግለሰቦች ብቃት፣የትግል(የድርጅት)ታማኝነት፣ ቁርጠኝነት፣ ተነሳሽነት፣ ፍላጎትና ቀጠናዊ እይታዎችን ከግምት ያስገባ ነበር፡፡
በዚህም መሰረት
1ኛ ኢ/ር ደሳለኝ ሲያስብ ሸዋ-ዋና መሪ
2ኛ.ፋኖ መቶ አለቃ ልመንህ ሻውል ም/መሪ
3ኛ. ፋኖ ዳግማዊ አምደፅዮን የድርጅት ፅ/ቤት ኃላፊ
4ኛ ፋኖ አሸናፊ ምንዳ የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ
5ኛ.ፋኖ ኢያሱ ሙሉጌታ ም/ድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ
6ኛ.ፋኖ ረ/ፕሮፍ.ማርከው መንግስቴ የአስተዳደር ጉዳዮች ኃላፊ
7ኛ.ፋኖ ኢ/ር ብዙአየሁ ደጀኔ ም/አስተዳደር ጉዳዮች ኃላፊ
8ኛ. ፋኖ ንጋቱ ይታፈሩ የፖለቲካ መምሪያ ኃላፊ
9ኛ.ፋኖ ኢ/ር ብሩክ ስለሽ የውጭ ጉዳይ መመሪያ ኃላፊ
10ኛ. ፋኖ ተስፋማርያም ታፈሰ ም/ውጭ ጉዳይ ምሪያ ኃላፊና ቃላቀባይ
11ኛ.ፋኖ አንድነት ይሁኔ ጥናትና እስትራቴጂ መምሪያ ኃላፊ
12ኛ. ፋኖ ለገሰ አየናቸው ም/ህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ
13ኛ. ፋኖ አክበር ስመኘው የፋይናንስና ግዥ መመሪያ ኃላፊ
14ኛ. ፋኒት አበበች ወንድምሁን ም/ሴቶች ጉዳይ መመሪያ ኃላፊ
15ኛ. ፋኖ ደረሰ ታደሰ አደረጃጀት መምሪያ ኃላፊ
16ኛ. ፋኖ አንዳርግ አሰፋ ም/ትምህርትና ስልጠና መመሪያ ኃላፊ
17ኛ.ፋኖ አበበ ፀጋዬ የሀብት አሰባሰብ መመሪያ ኃላፊ
19ኛ.ፋኖ ዳዊት ቀፀላ ቀጠናዊ ትስስር መመሪያ ኃላፊ
20ኛ.ፋኖ ተስፋየ ገስጥ የፍትህ ጉዳዮች መመሪያ ኃላፊ
21ኛ. ፋኒት ገነት ጥበቡ ሰነድና ታሪክ መመሪያ ኃላፊ
22ኛ.ፊትአውራሪ ባዩ አለባቸው ወታደራዊ ዋና አዛዥ
23ኛ.ፋኖ ሃምሳ አለቃ ካሳጌታቸው ም/አዛዥ ለኦፕሬሽን
24ኛ.ፋኖ ሃምሳ አለቃ ይርጋ ወንዳለ ም/አዛዥ ለአስተዳደር
25ኛ. ፋኖ መኮንን ማሞ ም/አዛዥ ለሎጀስቲክ
26ኛ. ፋኖ ንጉስ ደርብ ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ
27ኛ.ፋኖ ሞገስ መላኩ ኢንዶክትርኔሽን መምሪያ ኃላፊ
በማድረግ ሽግሽግ የተደረገና አዲስ አመራሮች የተመደቡበት እና የተቀረው በነበረበት ኃላፊነት የፀደቀበትና 2ኛው መደበኛ ጉባኤ ከላይ በዝርዝር የሰፈሩት ጭብጦች ላይ በስፋትና ጥልቀት ተወያይቶ የጋራ ውሳኔ ካሳለፈ በኃላ የሚከተለዉን መልእክት ለኢትዮጵያ ህዝብ በማስተላለፍ የ14 ቀናት ጉባኤ ተጠናቋል፡፡
ውድ የሀገራችን ብሄርና ብሄረሰቦች በሙሉ፣ ሁላችሁም እንደምታዉቁት እኛ የአማራ ህዝብ እጅግ የከፋ ሰቆቋና መከራ ውስጥ እንገኛለን፡፡ የአብይ አገዛዝ በተደራጀና መንግስታዊ አጀንዳ በሆነ አቋም የሚያደርስብንን የዘር ፍጅት ሰማይና ምድር ይቁጠረው፡ሞሶሎኒ በኢትዮጵያ እንዳደረገዉ አብይ የብረት ለበስ ታንክና የድሮን ጥቃትን ጨምሮ ብዙ ብዙ ጭፍጨፋ አድርሶብናል፡፡ በዚህም የተነሳ እኛ የአማራ ህዝብና የአማራ ፋኖ በሸዋ ዘርን ለማትረፍ በዱር በገደል ኑሮ ከጀመርን አመታት አስቆጠርን፡፡ በርግጥ ያኔም በአድዋ እንደተቋጨ ታዉቃላችሁ… ዛሬም ይኸዉ እንደሚደገም እኛ እርግጠኛ ነን!!!አየህ ዘመዳችን! በእኛ የደረሰ በደልና ሰቆቃ መጠንና አይነቱ ይለያይ ይሆናል እንጂ ባንተም ሳይደርስ ቀርቶ አይደለም፡፡ ደግሞስ በትግራይ የደረሰዉና እየደረሰ ያለው በደልና ግፍ ብሎም በኦሮሞ ህዝብ እየታየ ያለው ስቃይ መረዳት እንዴት ይከብዳል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማስ ቢሆን የሚደረገው ማፈናቀልና ደሀን የማጥፋት ፕሮጀክት ብሎም አፈና የአደባባይ ሚስጥር አደለምን? በመሆኑም ይህንን ለሰው ዘር ጸር የሆነ የሰይጣን አገዛዝና አስተዳደር ለማስወገድ ብሎም ህዝባችሁን ከበደል ለመታደግ ትግላችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉና በጋራ እንድንሰራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ሲሉ መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል።
ክብር ለተሰውት!
“ድላችን በክንዳችን”
የአማራ ፋኖ በሸዋ የህዝብ ግንኙነት ክፍል
ጥር 3/2017 ዓ/ም
ሸዋ አማራ ኢትዮጵያ