
ከአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ አማራ) የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
ሕዝባችን ባላፉት ሃምሳ (50) ዓመታት እውነተኛ የድርጅት መሪ፣ እውነተኛ የድርጅት አባል እንዲሁም እውነተኛ ርዕዮተ ዓለም ያለው እውነተኛ ድርጅት ኖሮት አያውቅም ወይም የነበሩት በአጭር ቀርተዋል። ፕሮፌሰር አስራት የተመሰረቱት እውነተኛው የመላው አማራ ሕዝባዊ ድርጅት (መአሕድ) የአማራን ሕዝብ በማይወክለው በብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ተጠልፎ ሲወድቅ በቁርጥ ቀን የአማራ ወጣቶች በ2010 ዓ.ም ተመስርቶ የነበረው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ደግሞ በሆዳምና አርቆ ማስተዋል ባቃታቸው አመራሩ ተጠልፎ ጠቅላላ ጉባዔ እንኳ ማድረግ ያቃተው ሆኖ በአገዛዙ የእህትነት ማዕረግ ተሰጥቶ የብልፅግና ፓርቲ እህት ፓርቲ ሆኖ አመራሩም ርዕዮቱም በልፅጓል። ከዚህም የተነሳ ያለፈውን የትርክት ዕዳ ለመቀልበስ፣ በየዕለቱ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማሳሳት፣ የዘር ማጽዳትና የዘር ፍጅት ለማስቆም፣ በሀገሪቱ ሥርዓተ መንግሥት ተገቢውን ሕዝባዊ ውክልና ለሕዝባችን ለመስጠትና የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት ያለምንም ስጋት እንዲቀጥል የሚያደርግ እውነተኛ ድርጅት ለመፍጠር የአማራ ፋኖ ከታች ወደላይ በሆነ የድርጅት አመሰራረት ሂደት እየሰራና ፋሽስቱን ሥርዓት እየታገለ መሆኑ ይታወቃል። ድርጅቱን በመፍጠር ሂደትም የሚቋቋመው የአማራ ፋኖ ድርጅት እንደመአሕድ ሕዝብን በማይወክል ድርጅት እንዳይተካ ወይም እንደአብን ሆዳምና አርቆ ማስተዋል በተሳናቸው መሪዎች እጅ እንዳይወድቅ በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በአራቱም ክፍለ ሀገራት ባሉ የፋኖ አደረጃጅቶች በኩል አንድ የፋኖ አደረጃጀት ለመፍጠር ብዙ ጊዜ ተሞክሯል። ከነዚም ውስጥ አንዱና ዋነኛው በሰኔ/2016ዓ.ም የተደረገው በዋነኝነት ይጠቀሳል። ይህም ሙከራ ራሳቸውን ለመሪነት ባጩ ግለሰቦችና ጥቂት ደጋፊዎቻቸው ተኮላሽቶ መጨናገፉ ገሀድ የወጣ እውነት ነው። የተንኮላሸውንና የሰኔውን ጭንጋፍ ግን በአቶ እስክንድር ነጋና ደጋፊዎቹ በኩል ሕይወት እንዲዘራ ተሞክሮ ሕይወት ባይዘራም የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) በሚል ስም ለሕዝብ ሊያስተዋውቁት ሞክረዋል፤ አመራርም መድበውለታል። አፋህድ ለምን ጭንጋፍ ሆነ? ቢባል ይህ ድርጅት የከሸፈው ከመነሻው የትግል መንታፊ በሆኑ ተረፈ-ብአዴናዊያንንና ትግሉን ለመሸጥ ዛፍ ስርም ቢሆንም ለመቀመጥ ዝግጁ በሆኑ ሆዳምና ስልጣን ናፋቂዎች እጅ ስለገባ ነው። የነዚህ አካላት ቀይ መስመር እውነተኛ ድርጅት መፍጠር ሳይሆን ለግል ጥቅማቸው በቂ የፍላጎት ማሟያ የሆነ ድርጅት እንዴት እንፍጠር የሚለው ነው። ይህ ድርጅት ታዲያ በአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ አማራ) ላይ ከሰሞኑ የሚዲያ ዘመቻ ከፍቶብናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የጠራውንና መሬት ላይ ያለውን እውነት ለሕዝባችንና ለደጋፊዎቻችን በሙሉ ማሳወቅ እንወዳለን።
በመጀመሪያ አፋህድ በቅጥፈት የሚታወቅና በተቀባይነት ቀውስ ውስጥ የወደቀ ድርጅት ነው። በአራቱም ክፍለ ሀገራት አለኝ ብሎ የሚገልጸው የሰራዊት መጠንና እያስተዳደርኩት ነው የሚለው ቀጠና በእጅጉ ከእውነት የራቀ ነው። የአፋህድ መሪዎች አንደሚሉት ከሆነ 2/3ኛውን የአማራ ፋኖ ኃይል በእነሱ ስር መሆኑን እና አብዛኛውን ነጻ የወጡ ቀጠናዎች እያስተዳደሩ መሆኑን ገልጸውልናል። እውነታው ግን በጎጃም ክፍለ ሀገር ምንም የሌላቸው ሲሆን በወሎና በጎንደርም በየክፍለ ሀገሩ ካሉት ፋኖዎች 5% የማይሆኑ መሆናቸው ነው። በሸዋም በአብዛኛው ቀጠና የሚንቀሳቀሰው ኃይል በአርበኛ ደሳለኝ ሲያስብሸዋ የሚመራ ሲሆን በአርበኛ መከታው ውስጥ ሆነውም ከሕዝባዊ ድርጅቱ አይደለንም የሚሉት በቀላል ቁጥር የሚገመቱ አይደሉም። በመሆኑም ድርጅቱ በገጠመው የአመራር ቀውስ፣ የፖለቲካ ርዕዮት፣ ዓላማና የአመለካከት ቀውስ ምክንያት የሚሰጠው መረጃ ማስረጃ-አልባ፤ የሚሰጠው ብያኔም እውነት-አልባ መሆኑን ሁሉም ታጋይና ሕዝባችን እንዲገነዘብልን እናሳውቃለን።
ድርጅቱ በነብርሃኑ ጁላ ተመራጭ ተደራዳሪ ተደርጎ መመረጡ ያስከተለበትን ኪሳራ፣ በዳውንት ቁጥቋጦ ስር የጀመረው ድርድር ያመጣበትን መዘዝ፣ ቅጥ አንባሩ የጠፋው ማኒፌስቶ ያስከተለውን የፖለቲካ አረዳድ የፈጠረው ቀውስ መሪዎቹን በየሚዲያው እየቀረቡ የሚዋሹትን ውሸት ለመሻገር ‘መሪ ልቀይር ነው’ እና ‘በፋኖ ተወጋሁ’ የሚለው ሀሳብ ከቀውስ ማምለጫ ድልድይ አድርጎ ስለተመለከታቸው በሁላችን ላይ ዋሸብን!!!
በአማራ ፋኖ የትግል ታሪክ የመጀመሪያዋን ጥይት በፋኖ ላይ (በነአርበኛ ደሳለኝ ሲያስብሸዋ ላይ) ያስተኮሰው የአፋህድ መሪ የሆነው እስክንድር ነጋ መሆኑ ለማንም የተሰወረ እውነት አይደለም። በመቀጠልም በአርበኛ ኮማንደር አሰግድ ላይም እንዲሁ ዘመቻ በመክፈት በጠላት እጅ እንዲወድቅ ያደረገውም ጭንጋፉ አፋህድ መሆኑ ይታወቃል። ለነገሩ የአማራን ታጋይ እያካለቡ ከትግል ሜዳ ሲገፉ ለነሱ ጽድቅ ነው። ትግል ሲጠልፉና የአማራን ሕዝብ የፋኖ ትግል ቁልቁል ሲሰዱም የፖለቲካ ምሁርነታቸውና ብፁዕነታቸው ነው ቀድሞ የሚነገር። በወንድም ላይ መተኮስን የምንፀየፈው ተግባር ስለሆነ ነው እንጅ በመጀመሪያ ያየነውም የተማርነውም ከእነሱ ከራሳቸው እየገረፉን ከሚያለቅሱት ነው። በመሆኑም ከሰሞኑ የአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ አማራ) በኮ/ል ፈንታው ሙሀቤና የሚመራው ሠራዊት ላይ ተኩስ ከፈቱብን ብሎ አፋህድ የለቀቀው መረጃ/መግለጫ ጊዜውን ጠብቆ ከሚለቃቸው ውሸቶቹ ውስጥ አንዱ ነው።
ድርጅቱ በተፈጠረበት የአመራር ቀውስና የአመራር ንዝህላልነት ምክንያት ከብልጽግና ጋር መደራደር መጀመሩን እንደመታረቅ ስለቆጠረው ሰራዊቱን የተለመደውን የወታደራዊ የወትሮ ዝግጁነት ባሕሉን ስላስቆሙት ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ በጠላት ከበባ ውስጥ እየገባ ቀላል የማይባል ሰራዊት ተሰውቷል፣ ተማርኳል፤ ከዲሽቃ ጀምሮም ብዙ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን አስማርኳል። አንዳንድ የውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት ከሆነም ድርድሩን በድርጅቱ ስር ያለው ሰራዊት ስለማይቀበለው ሰራዊቱን በዚህ መንገድ መቀነስና ማስወገድ የድርድራቸው አካል ሊሆን ይችላል!! ይህንን የመሪነት ግዴታቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸውን ወይም ከጠላት ጋር መስራታቸውን ለመሸፈን በሰራዊታቸው ላይ የሰሩትን ድራማ በድርጅታችን በአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ አማራ) ላይ ለማላከክ የሄዱበት ርቀት ደግሞ በእጅጉ ያሳዝናል። በእነሱ ስር ያለውን ሰራዊት በሴራ ማፍረሳቸው እንዳይበቃ ሌሎች ጠንካራ ድርጅቶች ላይ በመግባት ጥርጣሬን ለመዝራት ይሞክራሉ። የአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ አማራ) በማንም ላይ አልተኮሰም፤ ወደፊትም አይተኩስም። ነገር ግን አሁን በወሎ (ቤተ አማራ) ከመጣው አንድነታችን ጋር ተያይዞ እና መሪዎቻቸው የሚሰሩባቸውን ሴራ መቋቋም ሲያቅታቸው ድርጅታችንን የሚቀላቀሉ የሰራዊት አባላት አሉ፤ እነሱንም እየተቀበልን እንገኛለን፤ ይህ ሥራችንም ይቀጥላል።
ሌላውና አሳዛኙ ነገር አፋህድ የተፈጠረበትን ቀውስ ለማስቀየስ እና የሕዝብን ስሜት ይይዙልኛል በሚል የምስራቅ አማራ ፋኖ ለሁለት ዓመታት ሲዋጋው የነበረውን “ሕወሓትን” እንዲሁም “የወልቃይትንና የራያን” አጀንዳ መጎተቱና ለውስጣዊ ቀውሱ መሸፋፈኛነት መጠቀሙ ነው። በመጀመሪያ በአማራነታችን ፋኖነትን አቀጣጥለን የአማራን ሕዝብ ዳግም ወደነፍጡ የመለስንን የታሪክ ባለውለታዎች ረስቶና ሌላ ማንነት ሰጥቶ የራያም ሆነ የወልቃይት ባለቤት መሆን አይቻልም፤ ሲቀጥል የራያም ሆነ የወልቃይት ሕዝብ የሚፈልጉት በተግባር የሚገለጽ ድጋፍ የሚያደርግ ድርጅትን እንጅ ሲከፋን ሲከፋን ብቻ የምናነሳቸው አጀንዳዎችም አይደሉም፤ አማራነቱን በይፋ የማይቀበል የአማራ ድርጅት አመራርም በአማራነታችን ሊከሰን አይችልም፤ ይሄ አጀንዳ-አልባነት ነው። የፓለቲካ ርዕዮቱ፣ የፖለቲካ ዓላማና ግቡ እንዲሁም አመለካከቱ የተቀላቀሉበት ድርጅት አንዱ መገለጫው አጀንዳ-አልባነት ነው። በዚህም ምክንያት በሕዝብ እየተተፋ ያለው ድርጅቱ ላልቆመላቸው ወገኖቻችን አላኝታነቱን ማሳየቱ፣ በርዕዮቱ ያልቀረጸውን አጀንዳ ለመከራከሪያነት መቅረጹና መያዙ እንዲሁም ሕዝብን ለማወናበድ መሞከሩ ውድቀቱን የሚያፋጥነው ይሆናል።
ለአማራ ሕዝብ ግልጽ እንዲሆንለት የምንፈልገው ጉዳይ ግን በአማራ ትግል ውስጥ (ከሚኮንኑን ውጭ) ማንም የሕወሓትን አጀንዳ ለማስፈጸም የተቀመጠ የሕወሓት ተላላኪ የለም፤ ከሕወሓት ጋር የሚሰራ አካልም የለም። ነገር ግን የአማራ ሕዝብና የትግራይ ሕዝብ ከዚህ ቀደም እንደተፈጠረው በፌደራል መንግሥቱ አስተባባሪነትም ሆነ በሌላ ኃይል አስተባባሪነት ዳግም ወደጦርነት መግባት የለባቸውም። የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሔሮች ጋር ሆነው ኢትዮጵያ የሰሩ ሕዝቦች ናቸው ከዚህ በዘለለ ሁለቱ ሕዝቦች በባሕል፣ በሃይማኖትና በልዩ ልዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች የተሳሰሩ ሕዝቦች ስለሆኑ በመነጋገር ጥቅማቸውን ማስከበር ይችላሉ። የወልቃይትና የራያንም ጉዳይ ከጦርነት ባሻገር ባሉ መንገዶች መፍታት ይቻላል ብለን እናምናለን። በትግራይ ሕዝብም በኩል ተመሳሳይ ሀሳብ ይኖራል ብለን እናምናለን።
ብልጽግናና የብልጽግና የሚዲያ ተከፋዮች የድርጅታችንን መሪ ዋርካው ምሬ ወዳጆን መቀሌ አይደር ሆስፒታል ታክሞ መጣ እያሉ ሲያስወሩ ከርመው ተቀባይነት ቢያጡም አፋሕድ ተብየው የብልጽግና አጀንዳ ተሸካሚ ደግሞ ደቡብ ወሎ ደላንታ ወረዳ ፀሀይ መውጫ ከተማ ላይ ሰራዊቱን ሲያስጨፈጭፍና ሲያስማርክ የደረሰበትን ኪሳራ በሕወሓት ሰራዊት የደረሰብኝ ነው ብሎ ማሰቡ ኮ/ል ፈንታው በወንድም ላይ ካደረሰው ተደጋጋሚ በደል አንዱ ነው።
ስለዚህም:-
1ኛ. በድርጅታችን ያልታቀፋችሁ በወሎ ቀጠና የምትንቀሳቀሱ የፋኖ ሰራዊት አባላት በሙሉ
በሕዝባችንንና በእናንተ መስዋዕትነት የሚነግዱ፣ የድርጅታቸው ዓላማቸውና የታጋዩን ዓላማ የሚያወናብዱ ወልቃይትና ራያን ብቻ ሳይሆን መላውን ሕዝባችንን ለባርነትና ገባርነት እንዲሁም የአባቶቻችንን ሀገር ለጎሳው ርስትነት ከሚፈልገው የብልጽግና መንግሥት ጋር ከሚደራደሩ፣ የአገዛዙ ጄኔራሎች ጋር ከሚመካከሩ እና የብአዴን ብልጽግና አባላት ከሆኑ የአፋህድ አመራሮችና ሰርጎ ገቦች ራሳችሁን ነጻ በማውጣት ትግላችሁንና ታጋዩን ትጠብቁ ዘንድ እናሳስባችኋለን። ወንድማችንና የትግል ጓዳችን ኮሎኔል ፈንታውም በ20 ወራት ብቻ ከሰባት በላይ ድርጅቶችን ከመቀያየር የፋኖ ትግል በጀመርክበት ድርጅትህ ጸንተህና ተመልሰህ ወደወንድሞችህ ተቀላቅለህ እንድትታገል የትግል ጥሪ እናቀርብልሃለን።
2ኛ. ለመላው የአማራ ሕዝብና ደጋፊዎቻችን በሙሉ፦
አማራ ነኝ ብለው መናገር የማይደፍሩ ነገር ግን “አማራ አይደለህም” ብለው እውነተኛ ታጋይን ለማሸማቀቅ ማንም የማይቀድማቸው፣ መናገሻ ከተማችንን ሸዋን (አዲስ አበባን) የአማራ አይደለም ብለው የሚመሰክሩ ነገር ግን ስለወልቃይትና ራያ የአማራ ግዛትነት ሊያስታውሱን የሚወዱ እንዲሁም የአማርኛ ቋንቋ አመጣጥን ከመጤነት ጋር የሚያገናኙ ግለሰቦች ትግልህን ጠልፈው ለመጣል እየታተሩ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም የአማራ ፋኖ አንድ ወጥ አደረጃጀት ይዞ እስኪመጣ ድረስ በየክፍለ ሀገሩ ያሉ አደረጃጀቶችህን፣ ታጋይህንና ትግልህን እንደወትሮው ሁሉ እንድትጠብቅ እናሳስብሃለን። በመሆኑም ሰራዊት ሲፈርስባቸውና ማህበራዊ መሰረታቸውን ሲያጡ በታጋዮቻችን፣ በመሪዎቻችንና በድርጅታችን ላይ የሚዘምቱ አካላትን ባሉህ ባሕላዊ አደረጃጀቶች እንድታወግዝ፣ በተሳሳተ ጎዳና የሚገኙ ልጆችህንም ወደትክክለኛው የትግል መስመር እንድታስገባ እናሳውቅሃለን።
3ኛ. በውጭ ለምትገኙ የአማራ ተወላጆች፣ የትግሉ ደጋፊዎችና የሚዲያ አካላት በሙሉ፦
የማንነት ቀውስ የገጠማቸው ግለሰቦች፣ የርዕዮት ፈትነት የገጠመው ድርጅት እንዲሁም የሚታገሉለትን ሕዝብ ስምና የሚታገሉትን ጠላት ማንነት ያልተገለጠላቸውን ታጋይና አታጋዮች በስማቸውና በግብራቸው እንደምታውቋቸውና እውነተኛ ዓላማቸውንም እንደምትረዱት እንገነዘባለን። ነገር ግን በአማራ ሕዝብ ስም መነገድ፣ በታጋዩ ስም መገለጥና በአማራ ሕዝብ ጥቅም መደራደር በቃችሁ ሊባሉ ስለሚገባ ታሪካዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ በአማራ ሕዝብ ስም እንጠይቃለን።
ክብር ለትግሉ ሰማዕታት!!!
ሕልውናችን በተባበረ ክንዳችን!!!
የአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ አማራ)
ወሎ፣ አማራ፣ ኢትዮጵያ!